ኢትዮጵያ የሀገራዊ ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ፣ የሕዝቦቿን ደኅንነት ለማረጋገጥ እና የልማት ጉዞዋን በሰላም ለማስቀጠል የመከላከያ አቅሟን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ በዕውቀትና በተቋማዊ ብቃት እያጠናከረች ነው። ለዚህም የአየር ኃይሏን የመዋጋት እና የመከላከል አቅም ማዘመን የሀገራችንን ደኅንነትና ብሔራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ አኳያ ወሳኝ ሚና አለው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ለሀገር ደኅንነት በቂ ዝግጅት ማድረግ የግጭትን ለመቀነስ እና ሰላምን ለማስጠበቅ ወሳኝ ነው። የመከላከያ አቅም ግንባታ ዋና ዓላማ ጦርነትን መጋበዝ ሳይሆን ሀገርን ከጥቃት መጠበቅ እና ሰላምን ማረጋገጥ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ዘመናዊ የጦር አውሮፕላኖችንና የአየር መከላከያ ሥርዓቶችን በማሟላት የአየር ክልሏን ደኅንነት ለማጠናከር የምታደርገው ጥረት የሀገራችንን ስትራቴጂያዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።
ከሩሲያ መንግሥት ጋር በተደረገው የወታደራዊ ትብብር ዘመናዊ የጦር ቴክኖሎጂ አቅምን ማሳደግ ለኢትዮጵያ የመከላከያ ዝግጁነት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው።
ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛቷ፣ በታሪኳ እና በቀጣናዊ አስፈላጊነቷ ከፍተኛ ሚና ያላት ሀገር እንደመሆኗ፣ ከሀገራዊ አቅሟና ከምትሸከመው ኃላፊነት ጋር የሚመጣጠን የመከላከያ ብቃት መገንባት ይጠበቅባታል።
ይህም በዘመናዊ መሣሪያዎች ግዢ ብቻ የሚገነባ ሳይሆን፣ በሰው ኃይል ሥልጠና፣ በቴክኖሎጂ ዕውቀት፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በተቋማዊ ዘመናዊነት የሚጠናከር ነው።
ሰላምና ደኅንነት ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ ለኢንቨስትመንት፣ ለመሠረተ ልማት ግንባታ እና ለሕዝቦች የተሻለ ኑሮ መሠረት ናቸው። ስለሆነም ሀገርን ከስጋት የሚጠብቅ ጠንካራ የመከላከያ አቅም መገንባት የልማት ውጤቶችን ለማስጠበቅ እና ለቀጣይ ትውልድ የተረጋጋች ሀገር ለማስረከብ የሚያስችል ቁልፍ ተግባር ነው።
የኢትዮጵያ የመከላከያ አቅምን ማዘመን የሀገራችንን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ ባሻገር የሰላም፣ የመረጋጋትና የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የሚያግዝ ስትራቴጂያዊ አቅጣጫ ነው። የዛሬ በቂ ዝግጅት፣ በዕውቀት እና በቴክኖሎጂ የሚገነባው አቅም ነገ የሀገርን ደኅንነት ለማስጠበቅና ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራ መሠረት ለመጣል ወሳኝ ነው።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: