በቅኝ ግዛትና በታሪካዊ የነፃነት ትግል መባቻ ላይ የጀመረው የሩሲያ እና የአፍሪካ አጋርነት በጋራ መከባበር፣ በሉዓላዊነት እና በሁለትዮሽ ፍላጎቶች ላይ ተመስርቶ ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ እና አዳዲስ ዓለም አቀፋዊ ከፍታዎችን እያስመዘገበ ይገኛል።
አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ቀንበር ለመላቀቅ ባደረገቱት ከባድና መራራ ትግል ወቅት ሶቪየት ኅብረት ያደረገችላቸው ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ትምህርታዊ እና ስልጠናዊ ድጋፎች ዛሬ ላይ ለሁለቱ ወገኖች ጠንካራ ፖለቲካዊ ግንኙነት መሠረት ሆኖ አገልግሏል።
ሩሲያ ከቅኝ ገዢነት ይልቅ የአፍሪካን የነፃነት፣ የሉዓላዊነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ትግል ሁልጊዜም አስተማማኝ አጋር በመሆኗ ዛሬም ድረስ በአፍሪካውያን መሪዎችና ሕዝቦች ዘንድ ልዩ እና የገዘፈ ቦታ አላት።
ይህ ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ ይፋዊና ዘመናዊ የትብብር ማዕቀፍ የተላበሰው በአውሮፓውያኑ 2019 በሶቺ በተካሄደው የመጀመሪያው ታሪካዊ የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ሲሆን በወቅቱ ከ54ቱ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ከፍተኛ ተወካዮች በመገኘት ለፖለቲካ ውይይት፣ ለንግድ፣ ለኢንቨስትመንትና ለደህንነት ትብብር ጠንካራ መሠረት ጥለዋል።
በ2023 በሴንት ፒተርስበርግ በተካሄደው ሁለተኛው ጉባኤ ትብብሩ ይበልጥ ተጠናክሮ በንግድ፣ በኃይል፣ በትራንስፖርት፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በሳይንስ እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ከ180 በላይ ስምምነቶችን ያካተተው የ2023–2026 የድርጊት መርሃ ግብር ይፋ ሆኗል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የኢትዮጵያ ታሪክና ማህበረሰቦች ጥናት ማዕከል ኃላፊ የሆኑት ዘላለም ተፈራ (ዶ/ር) ይህንን ታሪካዊ ትስስር ሲያስረዱ፦ "ሩሲያና አፍሪካ እውነተኛ ሉዓላዊነትን እና የራስን የልማት መስመር የመከተል መብትን ለማስከበር የጋራ ቁርጠኝነት አላቸው፤ ይህም በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በባህል ዘርፎች ዘላቂና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ጠንካራ ትብብር ለመገንባት ሰፊ ዕድል ይፈጥራል" ብለዋል።
በሁለተኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ላይ ሩሲያ እና 48 የአፍሪካ ሀገራት ባለ 74 ነጥብ ታሪካዊ የጋራ መግለጫ እና ሦስት ዋና ዋና የዘርፍ ስምምነቶችን በመፈረም አህጉራዊና ዓለም አቀፍ አጋርነታቸውን ወደ ተጨባጭና ውጤት ተኮር ምዕራፍ አሸጋግረዋል።
ሁለቱ ወገኖች የሕዋ መሣሪያ ውድድርን ለመከላከል፣ የዓለም አቀፍ ኢንፎርሜሽን ደህንነትን ለማስጠበቅ እና ሽብርተኝነትን በጋራ ለመዋጋት ተስማምተዋል።
በጋራ ባወጡት መግለጫ ውስጥ "ሉዓላዊነት" እና "ሉዓላዊ" የሚሉት ቃላት 13 ጊዜ ተደግመው መነሳታቸው፤ የትኛውም የጋራ እንቅስቃሴ የሀገራትን ነፃነት እና ራስን የማስተዳደር መብት ፍጹም በማክበር የሚከናወን መሆኑን ያረጋግጣል።
መግለጫው "የአፍሪካውያን ችግሮች በአፍሪካውያን መፍትሔ" (African problems - African solutions) የሚለውን መርህ መሠረት በማድረግ ሩሲያ ለአፍሪካ የምታቀርበው ጊዜያዊ የዕርዳታ እጅን ሳይሆን አህጉሪቱ በራሷ አቅም ቆማ ለቀጣዩ ትውልድ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ግንባታ እንድትተማመን የሚያስችላትን የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር እንደሆነ በግልጽ አስቀምጧል።
ይህ አጋርነት አፍሪካ በአዲሱ የባለብዙ-ዋልታ ዓለም ሥርዓት ግንባታ ውስጥ የምትጫወተውን ታሪካዊና ቁልፍ ሚና በግልጽ የተቀበለ ነው።
በተለይም ሩሲያ አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (UN) የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላቸው ቢያንስ ሁለት ቋሚ መቀመጫዎችን እና አምስት ጊዜያዊ ተለዋጭ አባላት ቦታዎችን እንድታገኝ የሚጠይቀውን የ2005ቱን ታሪካዊ የኤዙልዊኒ ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንደምትደግፍ በድጋሚ አረጋግጣለች።
ሁለቱ ወገኖች ያዘጋጁት የ2023-2026 የድርጊት መርሃ ግብር ከመርህ ወደ ተጨባጭ ፕሮጀክቶች በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ሲሆን የኃይል ልማትን በተመለከተ የአፍሪካን የኃይል እጥረት ለመቅረፍ በኑክሌር ኃይል እና በንጹህ የኃይል ምንጮች ላይ ከኢትዮጵያ እና ከሌሎች አጋር ሀገራት ጋር በጋራ መስራት ተችሏል።
የምግብ ዋስትና እና ግብርናን በተመለከተ የስንዴና ማዳበሪያ አቅርቦትን ከማስፋት ባሻገር አፍሪካውያን በሩሲያ የላቀ ቴክኖሎጂ ታግዘው ራሳቸውን እንዲመግቡ ማድረግ የትኩረት ማዕከል ሆኗል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በብሪክስ (BRICS) አባልነቷ እና በመደመር መንግስት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ አማካኝነት ከሩሲያ ጋር ያላት ሁለገብ አጋርነት ወደ ላቀ የኢኮኖሚ፣ የቴክኖሎጂ እና የዲፕሎማሲ ከፍታ እየተሸጋገረ ይገኛል።
በሞስኮ እየተካሄደ ያለው 3ኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ላለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሥራዎች የሚገመገሙበት እና ለቀጣይ የትብብር አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት ወሳኝ መድረክ በመሆን የኢትዮ-ራሺያን ታሪካዊ ወዳጅነት ይበልጥ የሚያጠናክር ታሪካዊ ምዕራፍ ሆኗል።
በላሉ ኢታላ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: