ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ምክር ቤት አባልነት ለመወዳደር ከአፍሪካ ብቸኛዋ ዕጩ ሀገር ሆና መቅረቧ ተገለጸ።
ይህም በዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ዘርፍ ለበርካታ ዓመታት ላበረከተችው የጎላ አስተዋጽኦ እና የአህጉሪቱን ጥቅም ለማስከበር ላላት ቁርጠኝነት የተሰጣትን ከፍተኛ እምነት የሚያንፀባርቅ መሆኑ ተመላክቷል።
ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) እና የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን (AFCAC) መስራች አባል እንደመሆኗ የዘመናት ተቋማዊ ልምድ፣ የቴክኒክ ብቃት እንዲሁም በአቪዬሽን ደኅንነት፣ ጸጥታ እና አቅም ግንባታ ረገድ የጎላ ታሪክ ያላት ሀገር ናት።
ሀገራችን አፍሪካን ከአውሮፓ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ እና ከእስያ ሀገራት ጋር ለማገናኘት በምትገኝበት ስትራቴጂያዊ አቀማመጥ በመጠቀም በኢትዮጵያ አየር መንገድ በስፋት በሚሰጡ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቶች እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚታወቁ የአቪዬሽን ስልጠና፣ ጥገና እና የካርጎ አቅሟ አማካኝነት ዓለም አቀፍ ትሥሥርን ማጠናከሯን ቀጥላለች።
ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ በሚኖራት አባልነት የዓለም አቀፉን የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ዓላማዎች ለማስቀጠል የበለጠ ደኅንነቱ እና ጸጥታው የተጠበቀ አቪዬሽንን ለማስፋፋት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጠናከር እንደምትሰራም ተገልጿል።
በተያያዘም “No Country Left Behind” የሚለውን ዓለም አቀፍ ኢኒሼቲቭ በመደገፍ ሁሉም ሀገራት ከዘላቂ የአቪዬሽን ዕድገት እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: