Search

ከዘመናት መንፈሳዊ ትሥሥር እስከ ባለብዙ-ዋልታ ዲፕሎማሲያዊ ከፍታ የኢትዮ- ሩሲያ ታሪካዊ እና ስትራቴጂካዊ አጋርነት

ሓሙስ ጥቅምት 19, 2019 21

በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ በጋራ መከባበር፣ በባህል እና በጂኦፖለቲካዊ ትብብር ላይ የተመሠረቱ ጥቂት የማይባሉ ግንኙነቶች አሉ።

ከእነዚህ መካከል የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ታሪካዊ ግንኙነት በልዩ ምዕራፍ የሚጠቀስ ሲሆን ይህ ቁርኝት በወቅታዊ የፖለቲካ ፍላጎት ብቻ የተገደበ ሳይሆን ከክፍለ ዘመናት በፊት በባህል፣ በሃይማኖት እና በሉዓላዊነት ጥበቃ ላይ የተመሠረተ ጠንካራ መሠረት ያለው ነው።

በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መካከል ያለው ግንኙነት መሠረቱ የጀመረው በሃይማኖታዊ እና በባህላዊ ትሥሥር ሲሆን ሁለቱም ሀገራት ረጅም ታሪክ ያለው የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች በመሆናቸው በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ወንድማማችነት ስሜት ተፈጥሮ ነበር።

በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ በነበሩት ዓመታት የሩሲያ መንፈሳውያን እና ተጓዦች ወደ ኢትዮጵያ በማቅናት የነበረውን ግንኙነት ያጠናከሩት ሲሆን ይህ ጥንታዊ መንፈሳዊ ትሥሥር ቀስ በቀስ ወደ ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዲሸጋገር መንገድ ከፍቷል።

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ የፖለቲካ እና የወታደራዊ ደረጃ የተሸጋገረው በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ሲሆን ኢትዮጵያ በ1888 ዓ.ም ከአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች ጋር ስታደርግ በነበረው ሉዓላዊነትን የማስከበር ተጋድሎ ሩሲያ ወሳኝ የዲፕሎማሲ፣ የሕክምና እና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጋለች።

በዓድዋ ጦርነት ወቅት የሩሲያ ቀይ መስቀል ማኅበር አባላት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ለቆሰሉ የኢትዮጵያ አርበኞች የህክምና እርዳታ የሰጡ ሲሆን ከዓድዋ ድል በኋላ በ1890 ዓ.ም ሁለቱ ሀገራት ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን መሥርተዋል።

በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በተለይም በደርግ ሥርዓት ዘመን ከ1960ዎቹ እስከ 1980ዎቹ መጨረሻ በኢትዮጵያ እና በወቅቷ ሶቪየት ሕብረት መካከል ያለው ግንኙነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ የተሸጋገረ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ወደ ሶቪየት ሕብረት በመሄድ በምህንድስና፣ በሕክምና፣ በውትድርና፣ በጋዜጠኝነት እና በልዩ ልዩ ሳይንሳዊ ዘርፎች የከፍተኛ ትምህርት ዕድል አግኝተው ለሀገራችን ዘመናዊ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክተዋል።

ዛሬ ላይ በኢትዮጵያና በሩሲያ ፌዴሬሽን መካከል ያለው ግንኙነት በብዙ ዘርፎች እጅግ እየተጠናከረ የሚገኝ ሲሆን ሁለቱ ሀገራት በሁለትዮሽ እና በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላቸው ትብብር በግብርና፣ በኃይል በተለይም በኒውክሌር ቴክኖሎጂ ለሰላማዊ አገልግሎት፣ በኢነርጂና በማዕድን ልማት ዘርፎች የጋራ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ የብሪክስ (BRICS) ስብስብ አባል መሆኗ ከሩሲያ እና ከሌሎች አባል ሀገራት ጋር ያላትን የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር አዲስ ዕድል ፈጥሯል።

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: