የጥቅምት ወር ማጠቃለያ በሆነው በዚህ ወቅት የሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ ወደ መኸር ማጠቃለያና ቀዝቃዛው የምዕራብ አውሮፓ የበረዶ ወራት የምትሸጋገርበትን ቅዝቃዜ እያስተናገደች ትገኛለች።
የሙቀት መጠኑ ከዜሮ በታች ዝቅ ባለበት እና የሞስኮን ታሪካዊ የክሬምሊን አደባባዮችና ጎዳናዎች ቀዝቃዛው የሰሜን ንፋስ በሚያሸብሩበት በዚህ ወቅት የከተማዋ የዲፕሎማሲ ምህዳር ግን በእጅጉ ሞቆ ይታያል።
በሞስኮ ኤግዚቢሽን ማዕከላትና በታዋቂ የስብሰባ አዳራሾች አካባቢ የአፍሪካ ሀገራት ሰንደቅ ዓላማዎች በደመቀ ሁኔታ ተሰቅለው የሚውለበለቡ ሲሆን፤ የ48 ሀገራት ልዑካን፣ የ22 ሀገራት መሪዎች እና የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እንቅስቃሴ በከተማዋ የጸጥታና የዲፕሎማሲ አውታሮች ላይ ልዩ ግርማ ሞገስ ፈጥሯል።
ይህ በቅዝቃዜ የተከበበ ነገር ግን በሞቃት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ውይይቶች የተሞላው የሞስኮ ድባብ አፍሪካና ሩሲያ ለአዲስ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ አጋርነት ያላቸውን ጽኑ ቁርጠኝነት በግልጽ የሚያሳይ ሁነት ሆኗል።
በሞስኮው ጉባኤ ከተንጸባረቁ ዋነኛ የፖሊሲ አቅጣጫዎች መካከል የፋይናንስ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የመጀመሪያውን ደረጃ ይይዛል። የሩሲያ እና የአፍሪካ ባንኮች ቀጥተኛ ግንኙነታቸውን እንዲያሰፉ በየሀገራቱ ቅርንጫፎችን እንዲከፍቱ እና በሀገር ውስጥ ገንዘቦች የሚፈጸሙ የክፍያ ሥርዓቶችን እንዲያጠናክሩ ጥሪ ቀርቧል።
በተለይም የማዕከላዊ ባንክ የፋይናንስ መልእክት ልውውጥ ሥርዓቶችንና የፓን-አፍሪካን የክፍያ ሥርዓት (PAPSS) በስፋት በመጠቀም የግብይት ወጪዎችን ለመቀነስ እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን ከፖለቲካዊ ጫናዎች ለመጠበቅ የታለሙ ሀሳቦች ቀርበዋል።
በንግዱ ዘርፍ በአውሮፓውያኑ 2025 የሩሲያና አፍሪካ የሁለትዮሽ የንግድ መጠን 27 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይህንን መጠን እጥፍ በማድረግ ከ50 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማድረስ ግብ ተጥሏል።
በጉባኤው ላይ የተንጸባረቀው የፖሊሲ አቋም እንደሚመላከተው የሩሲያ ኩባንያዎች የአፍሪካን ተፈጥሮአዊ ሀብቶች ጥሬ ዕቃ አድርጎ ከማውጣት ይልቅ በሀገር ውስጥ ማኑፋክቸሪንግ እሴት መጨመር፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የታክስ ገቢን በማሳደግ ላይ የተመሠረተ ፍትሐዊ አጋርነት ለመገንባት ፍላጎት እንዳላቸው ተገልጿል።
በትብብር መስኮች ረገድ በአሁኑ ወቅት በ16 የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ከ30 በላይ የኢነርጂ ፕሮጀክቶች በመተግበር ላይ የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በውኃ ኃይል ማመንጫዎች፣ በታዳሽ ኢነርጂ እና በኒውክሌር ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ የተደረጉ ስምምነቶች ይጠቀሳሉ።
በተለይም ተንሳፋፊ የኒውክሌር የኃይል ማደያዎችን ለመጠቀም የተደረጉ የመግባቢያ ስምምነቶች የቀጣናውን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ አዲስ መንገድ የሚከፍቱ ናቸው።
በግብርናው ዘርፍ በ2026 የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት ውስጥ 13 ሚሊዮን ቶን የግብርና ምርቶች፣ እህልና ማዳበሪያዎች ለ40 የአፍሪካ ሀገራት የቀረቡ ቢሆንም አፍሪካ ራሷን በምግብ የመመገብ አቅሟን እንድታሳድግ የምርጥ ዘር ብዜት፣ የግብርና ሜካናይዜሽን፣ የምርት ማከማቻና ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተላለፍ ቁርጠኝነት ተንጸባርቋል።
በሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ በሳይበር ደህንነት፣ በዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት እና በጤናው ዘርፍ እስከ 2029 የሚዘልቅ የዋና ዋና ወረርሽኞች መቆጣጠሪያ ፕሮግራም የተዘረጋ ሲሆን በትምህርቱ ዘርፍም በአሁኑ ወቅት በሩሲያ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ አፍሪካውያን ተማሪዎች ቁጥር 40 ሺህ መድረሱና ለ2026–2027 የትምህርት ዘመን የሚሰጠው የነፃ ትምህርት ዕድል ወደ 5 ሺህ 500 ማደጉ ተመላክቷል።
በመድረኩ ላይ በአፍሪካ ኅብረት በኩል በግልጽ እንደተመላከተው አህጉሪቱ የጥሬ ዕቃ ላኪና ያለቀላቸው ምርቶች ተቀባይ ሆና መቀጠል እንደማትፈልግ ገልጻለች።
ይልቁንም በዓለም አቀፍ የነዳጅና የግብርና ምርቶች አቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ እሴት የሚጨምሩ ፋብሪካዎች በሀገር ውስጥ እንዲገነቡ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲደረግ እና የሀገር ውስጥ ሙያተኞች እንዲሰለጥኑ ጥሪ ቀርቧል።
ከሩሲያ ጋር የሚደረገው የኢንዱስትሪ፣ የግብርና፣ የኒውክሌር እና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሽግግር የኢትዮጵያን የምግብና የዳታ ሉዓላዊነት የሚያረጋግጥ ሲሆን፤ በተለይም ሩሲያን በሕንድና ኢራን በኩል ከምሥራቅ አፍሪካ ጋር የሚያገናኘው የሰሜን-ደቡብ የትራንስፖርት ኮሪደር እውን መሆን ለኢትዮጵያ አማራጭ የንግድና የሎጂስቲክስ በር በመክፈት ብሔራዊ ጥቅሟን በዘላቂነት የሚያስጠብቅ ታላቅ አህጉራዊ አቅም እንደሚፈጥር ተመላክቷል።
በሰለሞን ገዳ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: