Search

ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር በመተባበር የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት ወደ ተግባራዊ ሂደት እየተሸጋገረች ነው፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ሓሙስ ጥቅምት 19, 2019 43

ኢትዮጵያ በኃይል ዘርፍ ከሩሲያ ጋር በመተባበር የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት ወደ ተግባራዊ ሂደት እየተሸጋገረች መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ3ኛው የሩሲያ - አፍሪካ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር በመተባበር ወደ ተግባራዊ ሂደት እየተሸጋገረች የምትገኘው የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ፣ በውኃ ኃይል ላይ በብዛት የተመሠረተውን የኢነርጂ ምንጭ በማብዛት ለኢኮኖሚ ልማት የሚያስፈልገውን የኃይል አቅርቦት ለማጠናከር እንደሚያግዝ አመላክተዋል።

የኒውክሌር ሳይንስ ከኃይል ማመንጨት በተጨማሪ የምግብ ብክነትን ለመቀነስና የካንሰር ሕክምናን ለማሻሻል ያለውን አስተዋጽኦም ጠቅሰዋል።

በዘርፉ የሚደረገው ትብብር ቴክኖሎጂውን በደኅንነት ለመጠቀምና ለመቆጣጠር የሚያስችል የሀገር ውስጥ ዕውቀት እና ሙያዊ አቅም ማዳበርንም ማካተት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ በዕውቀት እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ የሰው ሠራሽ አስተውሎት አቅሟን ለማሳደግ እየሠራች መሆኑን ጠቁመው፣ በአዲስ አበባ የመደመር የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ እየተቋቋመ መሆኑን ገልጸዋል።

የሩሲያ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት በማስተማር እና በምርምር ከኢትዮጵያ ጋር እንዲተባበሩም ጥሪ አቅርበዋል።

የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎች በዓለም የሚገኙ ቋንቋዎችን እና የሕዝቦችን ተሞክሮ በሚያንጸባርቁበት መንገድ ላይ የሚኖራቸውን ተጽዕኖ በማንሳት፣ አፍሪካዊያን በራሳቸው ቋንቋዎች ቴክኖሎጂዎችን መፍጠርና ተቋማትም መረጃዎቻቸውን እንዴት እንደሚጠቀሙ የመወሰን አቅም ማጎልበት እንዳለባቸው አስረድተዋል።

በኢንቲሃድ አብራር

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: