Search

የዳታ ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ ኢትዮጵያ የመደመር ሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ በማቋቋም ላይ ትገኛለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ሓሙስ ጥቅምት 19, 2019 77

ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ከተማ የመደመር ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ዩኒቨርሲቲ በማቋቋም ላይ መሆኗን ይፋ በማድረግ የሩሲያ ከፍተኛ የትምህርት እና የምርምር ተቋማት በመማር ማስተማር እና በጥናት ዘርፍ አብረው እንዲሠሩ ጥሪ አቀረበች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ3ኛው ሩሲያ - አፍሪካ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የአንድ ሀገር እውነተኛ አቅም የሚለካው በሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሉዓላዊነትን ጽንሰ-ሐሳብ ከተለመደው የድንበር ጥበቃ ትርጓሜ በማሻገር ከቴክኖሎጂ እና ከመረጃ (ዳታ) ባለቤትነት ጋር አያይዘውታል።

“ነፃነት የመወሰን መብት ይሰጠናል፤ አቅም ደግሞ ውሳኔዎችን ወደ ተግባር የምንቀይርበትን ጉልበት ይሰጠናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ሥርዓቶች የሚገነቡበት መንገድ የትኞቹ ቋንቋዎች አገልግሎት እንደሚያገኙ እና የማን ባህልና ልምድ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደሚወከል እንደሚወስን አስገንዝበዋል።

በዚህም መሠረት አፍሪካውያን ተመራማሪዎች በራሳቸው ሕዝቦች ቋንቋዎች የሚሠሩ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን የመፍጠር አቅም ሊኖራቸው እንደሚገባ በአጽንኦት ተናግረዋል።

በተጨማሪም አፍሪካውያን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ብቻ ከመሆን ወጥተው፣ አህጉራዊ ተቋማት እነዚህ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች የሕዝቡን መረጃዎች (ዳታ) እንዴት እንደሚጠቀሙ የመወሰን ሉዓላዊ ሥልጣን ሊኖራቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ይህንን የቴክኖሎጂ እና የዳታ ሉዓላዊነት እውን ለማድረግ በምግብ፣ በኢነርጂ እና በእውቀት ዘርፎች ላይ ስትራቴጂያዊ ኢንቨስትመንት እያደረገች ትገኛለች ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

አዲስ የሚቋቋመው የመደመር አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲም ከሩሲያ አቻ ተቋማት ጋር በሚፈጥረው የምርምር ትሥሥር፣ ሀገር በቀል ቋንቋዎችን እና የአፍሪካን ዳታ ማዕከል ያደረጉ ቴክኖሎጂዎችን ለማበልጸግ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ይጠበቃል።

በበረከት ሽመልስ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: