Search

የትግራይ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ በአዲስ ስያሜ የብሮድካስት ፈቃድ ተሰጠው

ሓሙስ ጥቅምት 19, 2019 69

በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ታግዶ የነበረው “የትግራይ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ”፣ “ትግራይ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን” በሚል አዲስ ስያሜ አዲስ የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ መሰጠቱን ባለሥልጣኑ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 1238/2013 በተሰጠው ሥልጣን እና ኃላፊነት መሠረት ባደረገው ክትትል እና ቁጥጥር፤ ቀደም ሲል የትግራይ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ የመገናኛ ብዙኃን አዋጁን የሚቃረኑ፣ ብሔራዊ ጥቅምን የሚጻረሩ፣ ጽንፈኝነትን የሚያበረታቱ እና የሀገርን እና የሕዝብን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ይዘቶችን ሲያሠራጭ በመገኘቱ ፈቃዱ ታግዶ መቆየቱ ይታወሳል።

የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር ቀደም ሲል በትግራይ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ ሲሰጥ የነበረው የብሮድካስት አገልግሎት የጦርነት እና የጥፋት ተልዕኮ ማስፈጸሚያ ሆኖ በማገልገሉ ምክንያት ፈቃዱ መታገዱን አስታውሷል።

አሁን ክልሉን የሚመራው ባለአደራ አስተዳደር የክልሉን ሰላም እና መረጋጋት በማረጋገጥ እንዲሁም የሕዝብ ድምፅ በመሆን አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንዲያበረክት “ትግራይ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን” በሚል አዲስ ስያሜ ተቀይሮ ፈቃድ እንዲሰጠው ጥያቄ ማቅረቡን ባለሥልጣኑ ጠቅሷል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቀረበለትን ጥያቄ ከመገናኛ ብዙኃን አዋጁ አንጻር በመመርመር ጥያቄው ተገቢነት ያለው መሆኑን በማመን የተቀበለው መሆኑን እና በዛሬው ዕለት አዲስ ፈቃድ መስጠቱን ገልጿል።

ባለሥልጣኑ “ትግራይ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን” በሚል አዲስ የብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ የሰጠ መሆኑን ያሳወቀ ሲሆን፣ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ለብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽኑ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪውን አስተላልፏል።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: