Search

“ለሁለንተናዊ ብልጽግና ሁለንተናዊ ዝግጁነት ያለው አመራር መገንባት ያስፈልጋል”፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ቅዳሜ ጥቅምት 21, 2019 75

የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ለመገንባት ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚገባ እና ለዚህ ደግሞ በአካል፣ በመንፈስ፣ በዕውቀት እና በጥበብ የዳበረ ሁለንተናዊ ዝግጁነት ያለው አመራር መገንባት ወሳኝ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሁለንተናዊ ብልጽግና ማለት ቁሳዊ እና መንፈሳዊ፣ ባህላዊ እና ሞራላዊ ብልጽግና የተሸመኑበት መሆኑን ገልጸው፤ አመራሩ በተለይም በሀገር ፍቅር ስሜት እና በሕዝብ ተቆርቋሪነት መንፈስ ግዴታዎቹን እንዲወጣ የሀገር አደራዋ ጥብቅ መሆኑን አስምረውበታል።

ወታደራዊ ሳይንስ፣ ልምድ እና ሕይወት የሰውን ልጅ ዓላማ እና ሰብእና በመቅረጽ ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዲሲፕሊን ያለው፣ ግዳጅን በብቃት የሚፈጽም፣ በዐርበኝነት መንፈስ የሚያገለግል እና የጋራ ግብን በጋራ የሚያሳካ ትውልድ ለማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አብራርተዋል።

ዐበይት የፖሊሲ እና የሥልጠና ነጥቦችን ሲዘረዝሩ የመደመር መንግሥት አመራሮች በሁርሶ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ሥልጠና በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ ይፋ ገልጸዋል።

በአንድ ሰዋሰው መግባባት፣ ሥነ ምኅዳርን በሚገባ መጠቀም፣ ሕዝብን ለዓላማ እና ለተግባር ማነጽ፣ ለሕዝብ የገባነውን ቃል አከናውኖ መጨረስ፣ መዋቅርን ለሀገራዊ ዓላማ ማሣለጥ፣ ሀገርን በባለ አደራነት መምራት፣ ተተኪ ትውልድን ማፍራት እና የሀገርን ደኅንነት ማረጋገጥ የሥልጠናው ዋና ዋና የስትራቴጂ ሐሳቦች ናቸው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።

“ወታደሮች ዒላማ፤ ሲቪሎች ደግሞ ዓላማ አላቸው፤ የሁለቱም ግብ ድልን ማስመዝገብ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሁለቱን ዲሲፕሊኖች በማገናዘብ ዒላማውንም የሚመታ፣ ዓላማውንም የሚያሳካ ትውልድ እንደሚፈጠር አረጋግጠዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: