Search

የባሕር በር፡- ለመጪው ትውልድ የሚተርፍ ሀገራዊ ሀብት

ሰኞ ጥቅምት 23, 2019 44

ለታላቅ ሕዝብ፣ ለታሪክ ባለቤት እና ለገዘፈች ሀገር የባሕር በር ማጣት ምን ትርጉም አለው? ይህ መሠረታዊ ጥያቄ የሀገራችንን የታሪክ ጉዞ፣ የኢኮኖሚ አቅም እና የሕልውና ጉዳይ በቀጥታ የሚፈትን ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ እንደሚያነሱት፣ የባሕር በር ጥያቄ የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ከሚወስኑ ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ቀዳሚው ነው።

ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ሀገር ቀጥተኛ የባሕር በር አለመኖር በንግድ እንቅስቃሴ፣ በኢኮኖሚ ዕድገት እና በስትራቴጂያዊ ደኅንነቷ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል።

ሀገራችን በየዓመቱ ለወደብ ኪራይ እና ለሎጂስቲክስ የምታወጣው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለትምህርት፣ ለጤና እና ለመሠረተ ልማት ሊውል የሚችል ግዙፍ ሀብት ነው። ይህ የተንዛዛ የሎጂስቲክስ ወጪ በምርት ዋጋ መናር እና በዓለም አቀፍ የንግድ ተወዳዳሪነታችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል።

የሕዝብ ቁጥራችን በፍጥነት እያደገ ባለበት እና የልማት ፍላጎታችንን ማሟላት ግድ በሚልበት በዚህ ወቅት፣ የባሕር በር አለመኖር የወደፊት ዕቅዶቻችንን የሚያደናቅፍ ፈተና ነው።

በመሆኑም የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የአሁኑ ትውልድ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን፣ ለመጪው ትውልድ ጠንካራ ሀገራዊ አቅም የመገንባት የሕልውና ጉዳይ ነው።

ይህንን ጫና በመገንዘብም የመደመር መንግሥት ለመጪው ትውልድ የሚሻገር ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግን በዋና ሀገራዊ ግብነት ይዞ በትኩረት እየሠራ ይገኛል። ኢትዮጵያ የባሕር በሩን ለማግኘት የምታደርገው ጥረት የውስጥ ኢኮኖሚ አቅሟን ከማጠናከር ባሻገር፣ በቀጣናው ያላትን የጂኦፖለቲካዊ ሚና ሚዛናዊ የሚያደርግ ነው።

ይህ ጥያቄ በማንም ላይ ስጋት ለመፍጠር የተነሳ ሳይሆን፣ የሀገራችንን ኢኮኖሚያዊ ደኅንነት ከቀጣናው የጋራ ብልጽግና ጋር ለማስተሳሰር የሚደረግ ትክክለኛ ጥረት ነው። ትሥሥሩ በሰላማዊ ውይይት እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመሥርቶ ሲተገበር፣ ለንግድ ልውውጥ፣ ለኢኮኖሚ ውህደትና ለአካባቢው ሰላም መረጋገጥ የጎላ አበርክቶ ይኖረዋል።

አስተማማኝ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ኮሪደሮች መዘርጋት አምራቾችን ከዓለም ገበያ ጋር ከማገናኘት ባለፈ በመስመሮቹ ላይ ለሚገኙ ማኅበረሰቦች የኢኮኖሚ መነቃቃትን ይፈጥራል። በተለይም አሁን ወደ ተግባር እየገባ ካለው የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ጋር ሲናበብ ሰፊ የንግድ ትሥሥርን ያበረታታል።

ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጋር ያላት ታሪካዊ ቁርኝት በጂኦግራፊያዊ ቅርበት ብቻ የተገደበ ሳይሆን፣ በዘመናት የንግድ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እና የቀጣናዊ ትብብር ታሪክ ላይ የተገነባ ነው። ይህንን ታሪካዊ ትሥሥር በዘላቂ የኢኮኖሚ አጋርነት ማደስ ለሀገራችን ብልጽግናም ሆነ ለቀጣናው የጋራ ዕድገት ወሳኝ ምሰሶ ነው።

በመሆኑም የባሕር በር ለመጪው ትውልድ የሚሸጋገር ጠንካራ ሀገራዊ አቅም የመገንባት፣ የኢኮኖሚ ደኅንነትን የማረጋገጥ እና የሉዓላዊነት ጉዳይ ነው። ይህ ፍትሐዊ ጥያቄ በሰላማዊ ውይይት፣ በሕጋዊ ማዕቀፍ እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመሥርቶ ምላሽ ሲያገኝ፣ ለሀገራችን ዘላቂ ብልጽግና ብቻ ሳይሆን ለመላው ቀጣና አስተማማኝ ሰላምና ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

በኢንቲሃድ አብራር

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: