በመቐለ ከተማ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በፍጥነት ለማስጀመርና የህዝብን የእለት ተእለት ፍላጎት በዘመናዊ መልኩ ለማሟላት የሚያስችል ውይይት ተካሂዷል።
የፌደራል የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አመራሮች እና ሞያተኞች በመቐለ ከተማ በመገኘት አገልግሎቱን እውን ለማድረግ ከከተማዋ ባለአደራ አስተዳደር አመራሮች ጋር የተመካከሩ ሲሆን ይህም በትግራይ ክልል የተጀመረውን የሰላም ተስፋና ሀገራዊ የልማት ትስስር በተግባር ያረጋገጠ ምዕራፍ ሆኗል።
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የፌደራል የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ዮናስ አለማየሁ እንደገለጹት አሁን ላይ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተዋል።
በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት 114 አገልግሎቶችን በአንድ ጣሪያ ስር መስጠት የተቻለበት ደረጃ ላይ በመደረሱ የዜጎች እርካታ 99 በመቶ መድረሱንም ጠቅሰዋል።
በሁሉም ክልሎች ይህ አሰራር በስፋት እየተተገበረ የሚገኝ ሲሆን በነበረው ነባራዊ ሁኔታ በትግራይ ክልል እስካሁን ሳይጀምር ቢቆይም አሁን ላይ የባለአደራ አስተዳደሩ አገልግሎቱን ለማስጀመር ያሳየውን ቁርጠኝነትና ዋና ስራ አስፈፃሚው አድንቀዋል።
የመቐለ ከተማ ከንቲባ ሺሻይ አማረ (ዶ/ር) በበኩላቸው በሌሎች አካባቢዎች የታየው ፈጣንና ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥ በመቐለ ከተማም በፍጥነት እንዲጀምር በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በሌሎች ሀገራዊ አካባቢዎች በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የታየው የፈጣን አገልግሎት አሰጣጥ ተሞክሮ በትግራይ ክልልም በፍጥነት ሊተገበር እንደሚገባ ያነሱት ከንቲባው የፌደራል የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች፣ ስልጠና በመስጠትና የዕውቀት ሽግግር በማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም በሌሎች የትግራይ ክልል አካባቢዎች ለሚገነቡ ማዕከላት በመቐለ ከተማ የሚሰራው አሰራር መነሻ ስለሚሆን በፍጥነት፣ በጥራትና በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በአስማረ ብርሃኑ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: