Search

የሀገር አደራ እና የአመራር ጥብቅ ኃላፊነት በሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ

ሰኞ ጥቅምት 23, 2019 40

ሀገር ሲነሣ የትውልድ ትዝታ፣ የታሪክ ውርስ እና የነገ ተስፋ በአንድነት ይሰባሰባሉ። ሀገርን ማጽናት፣ የሕዝብን ደኅንነት እና ልማት ማረጋገጥ የፖለቲካ ወይም የየዕለት ሥራ ብቻ ሳይሆን፣ ከሁሉም በላይ የተቀደሰ የሞራል እና የታሪክ አደራ ነው።

በዚሁ መነሻ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “አመራሩ በሀገር ፍቅር ስሜት እና በሕዝብ ተቆርቋሪነት መንፈስ ግዴታዎቹን እንዲወጣ የሀገር አደራዋ ጥብቅ ነው” በማለት ያስተላለፉት መልዕክት፣ ለአሁኗ ኢትዮጵያ ወሳኝ እና ወቅታዊ አቅጣጫን አመላካች ነው።

የሀገር አደራ ክብደት የሚለካው ከሚሰጠው ሥልጣን ስፋት አንጻር ሳይሆን፣ በሕዝብ ሕይወት፣ ደኅንነት እና የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ በሚኖረው ቀጥተኛ ተጽዕኖ ነው።

ኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገረችው በአባቶች እና እናቶች ጥብቅ ጽናት፣ አብሮነት እና ለሀገር ባላቸው ጥልቅ ፍቅር ነው። ይህንን ውርስ ማስቀጠል ዛሬ ላይ ለተቀመጠው መሪም የማይቀር ኃላፊነት ነው።

መሪ ማለት የራሱን ጥቅም እና ምቾት ቅድሚያ የሚሰጥ ሳይሆን፣ የሕዝብን ዕንባ የሚያብስ፣ የዜጎችን ሰላም እና ልማት እንደ ዐይን ብሌን የሚጠብቅ ነው። የዚህ አደራ ጥብቅነት የሚመዘነው መሪው ከግል ፍላጎት ወጥቶ ለሕዝብ ጥቅም ሲል በሚከፍለው የቁርጠኝነት ዋጋ ነው።

በማንኛውም የሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ የሀብት አቅርቦት እና የስትራቴጂ ማዕቀፎች አስፈላጊ ናቸው። ይሁን እንጂ ከእነዚህ ሁሉ በላይ መሠረቱ የሀገር ፍቅር ስሜት ነው።

የሀገር ፍቅር ስሜት ያለው አመራር ፈተናዎች ሲያጋጥሙት ተስፋ አይቆርጥም፤ ይለዋወጣል እንጂ ከግቡ አይንሸራተትም። ችግሮችን እንደ ዕድል በመጠቀም መፍትሔዎችን ለመፈለግ ያነሳሳዋል።

በሕዝብ እና በአመራር መካከል ጠንካራ መተማመን እንዲፈጠር የሚያደርገው የአመራሩ ታማኝነት እና ለሀገር ያለው ቅንነት ነው። ሕዝብ መሪውን የሚያምነው የሀገሩን ደኅንነት በእጅጉ እንደሚያስብ ሲረዳ ነው።

ኢትዮጵያ ዛሬ በርካታ የኢኮኖሚ፣ የሰላም እና የልማት ውጥኖችን እያከናወነች ትገኛለች። እነዚህን ከግብ ለማድረስ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ሕዝብን በታማኝነት እና በፍትሐዊነት ለማገልገል የገባውን ቃል በሥራ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።

የሀገር አደራ በግለሰብ ጥረት ብቻ የሚሰምር አይደለም። የጋራ ዕይታን በመያዝ፣ በቅንጅት እና በግልጽነት መንፈስ መንቀሳቀስ የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። የዛሬው አመራር ውሳኔ ለነገው ትውልድ ታሪክ ይጽፋል። በመሆኑም የተሰጠውን አደራ በታላቅ ኃላፊነት ስሜት መወጣት የሕልውና ጉዳይ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት እንደሚያስገነዝበን፣ የሀገር ጉዳይ የሚለካው በንግግር ሳይሆን በተግባር እና በውጤት ነው። አመራሩ በሀገር ፍቅር ስሜት፣ በንቁ ተሳትፎ እና በከፍተኛ የሕዝብ ተቆርቋሪነት መንፈስ ሲንቀሳቀስ ብቻ ነው ሀገር ከፍ ብላ የምትታየው።

የሀገር አደራ ጥብቅ መሆኑ የቁጭት፣ የዕድገት እና የዘላቂ ሰላም ማረጋገጫ እንድትሆን የማድረግ ኃላፊነት የሁሉም መሪዎች የዕለት ተዕለት ተግባር ሊሆን ይገባል።

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: