Search

የዜጎችን መሠረታዊ ፍላጎት የማረጋገጥ ጉዞ፦ የምግብ፣ ቤት እና ትራንስፖርት ዘርፎች ትራንስፎርሜሽን በኢትዮጵያ

ሰኞ ጥቅምት 23, 2019 50

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የያዘችው የብልጽግና ጉዞም የሰዎችን የኑሮ ጫና በዘላቂነት የሚያቃልሉ ሦስት ዋና ዋና አዕማድ — ምግብን፣ ቤትን እና ትራንስፖርትን መሠረት ያደረገ መዋቅራዊ ትራንስፎርሜሽን ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በእነዚህ ስትራቴጂያዊ ዘርፎች የተጀመሩት አበረታች ሥራዎች በዜጎች ሕይወት ላይ መሠረታዊ ለውጥ እስኪያመጡ ድረስ ተጠናክረው ይቀጥላሉ።

ይህም መልእክት የሀገራችንን ሁለንተናዊ ዕድገት መሠረት የሚጥሉ ዋና ዋና የልማት አቅጣጫዎችን የሚያሳይ ነው፤ ምክንያቱም የማኅበረሰብ ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚረጋገጠው የዜጎች መሠረታዊ ፍላጎቶች በጥራት እና በዘላቂነት ሲሟሉ ብቻ በመሆኑ ነው።

የምግብ ዋስትና እና የግብርና ትራንስፎርሜሽን፦ የሉዓላዊነትና የሕልውና መሠረት

የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የዜጎች የሕልውና ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሀገር ሉዓላዊነት እና የነፃነት መሠረት ነው። ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የጀመረችው የምርትና ምርታማነት ማሳደግ እንቅስቃሴ የዜጎችን ሕይወት ከመቀየር ባለፈ ሀገራዊ ገጽታን በአዲስ መልክ እያነጸ ይገኛል።

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሀገራችንን ከምግብ እህል አራጅነት አውጥቶ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በመሸፈን ምርቱን ወደ ውጭ ሀገራት ኤክስፖርት ወደ ማድረግ ያሸጋገረ ታሪካዊ ስኬት ነው።

በሌላ በኩል የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ የጓሮ አትክልት፣ የዶሮ፣ የበግና ፍየል እንዲሁም የወተት ምርታማነትን በማሳደግ የዜጎችን የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት የሚያረጋግጥና የኑሮ ውድነትን በየደረጃው የሚታደግ ሀገራዊ እንቅስቃሴ ሆኖ ቀጥሏል።

በኩታ-ገጠም አስተራረስ፣ በመስኖ ልማትና በዘመናዊ ግብርና ቴክኖሎጂዎች የታገዘው ጥረት የሀገራችንን የምግብ ዋስትና በዘላቂነት ለማረጋገጥ ጽኑ መሠረት ጥሏል።

የመኖሪያ ቤት አቅርቦት እና የከተሞች ማሻሻያ፦ ጽዱና ምቹ ከባቢን የመፍጠር ራዕይ

ከተሞች በፍጥነት እያደጉ ባሉበት በዚህ ወቅት ለዜጎች ምቹ፣ ጽዱ እና ተመጣጣኝ የመኖሪያ ቤት ማቅረብ የመንግሥት ቀዳሚ ትኩረት ነው። የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች የከተሞችን የመሠረተ ልማት ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ በማሻሻል፣ ለዜጎች ምቹ የኑሮ፣ የሥራ እና የመዝናኛ ከባቢን በመፍጠር ረገድ መሠረታዊ የከተሜነት ባህል ለውጥ አምጥተዋል።

በተጨማሪም የመደመር መንግሥት የግሉንና የመንግሥትን አቅም በማስተባበር እንዲሁም የበጎ ፈቃደኞችን ርብርብ በማቀናጀት፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች የቤት ባለቤት ለማድረግና የመኖሪያ ቤት እጥረትን በዘላቂነት ለመፍታት 1.5 ሚሊዮን ቤቶችን የመገንባት ታላቅ ስትራቴጂያዊ ግብ አስቀምጦ ወደ ሥራ ገብቷል።

የትራንስፖርት እና ዘመናዊ መሠረተ ልማት፦ የኢኮኖሚው ዋና ደም ሥር

ቀልጣፋና ዘመናዊ የትራንስፖርት ሥርዓት የንግድ፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ዋና አንቀሳቃሽ ሞተር ነው። ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ማበረታታት እና በነዳጅ የሚሠሩ የሕዝብ አውቶቡሶችን ወደ ሀገር ውስጥ የተፈጥሮ ጋዝ ተጠቃሚነት ማሸጋገር፣ ለነዳጅ የሚወጣውን በቢሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ ከመታደጉም በላይ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።

ዘመናዊና ወጪ ቆጣቢ የሕዝብ ትራንስፖርት አማራጮችን ወደ አገልግሎት ማስገባት የዜጎችን የዕለት ተዕለት የእንቅስቃሴ እንግልት በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ነው።

በምግብ፣ በቤት እና በትራንስፖርት ዘርፎች የተመዘገቡት አበይት ስኬቶችና የተጀመሩት አበረታች ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸው የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ከማሻሻሉም በላይ ለሁለንተናዊ ሀገራዊ ብልጽግና ጽኑ መሠረት ይጥላሉ።

የመንግሥት ቁርጠኝነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እነዚህን ታላላቅ ሀገራዊ የልማት ግቦች ዳር ለማድረስ የማኅበረሰቡ፣ የግሉ ባለሀብት እና የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረትና አጋርነት ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል።

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: