በዘመናዊው ዓለም የሉዓላዊነት እና የሰላም ዋስትና በዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ውጫዊ ኃይል የሀገርን ድንበር ወይም የአየር ክልል ለመጣስ ሲያስብ ሁለት ጊዜ እንዲያስብ የሚያስገድድ አስተማማኝ የቅድመ-መከላከል አቅም (Deterrence Capability) ሲኖር ነው።
ኢትዮጵያ 12 ዘመናዊ የSu-35 ተዋጊ ጄቶችን እና አራት የS-400 የረጅም ርቀት የአየር መከላከያ ባትሪዎችን ከሩሲያ መረከቧ በሀገራችን ወታደራዊ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ የተሻገረ የስትራቴጂያዊ አቅም ግንባታ ማሳያ ነው። ይህም የሰላም ዋስትናን በጠንካራ ወታደራዊ ዝግጁነት ለማጽናት የሚደረግ ብሔራዊ እርምጃ ነው።
የሱ-35 ተዋጊ ጄቶች እና የS-400 የረጅም ርቀት የአየር መከላከያ ሥርዓቶች ሲጣመሩ ዘመናዊው ዓለም ሊያገኛቸው የሚችላቸውን ኃይለኛ የአየር መከላከል እና ማጥቃት አቅሞች ይፈጥራሉ።
የSu-35 ተዋጊ ጄቶች እጅግ የላቀ የአየር ላይ የበላይነት አቅም ያላቸው ሲሆን በረጅም ርቀት ራዳራቸው፣ በያዙት ቴክኖሎጂ አማካኝነት የሚሰጡት ከፍተኛ የመንቀሳቀስ ነፃነት እና በርካታ ዒላማዎችን በአንድ ጊዜ የመቆጣጠር አቅም አላቸው።
እነዚህ ጄቶች ከራሳቸው ድንበር ወጣ ብለው የአየር ክልልን ለመጠበቅ እና ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን አስቀድሞ ለመቀልበስ ያስችላሉ።
ኤስ-400 ከምድር ሆኖ ሰፊውን የአየር ክልል በጥብቅ ሲቆጣጠር እና የጠላት አውሮፕላኖች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይጠጉ ከለላ ሲሰጥ ሱ-35 ደግሞ በአየር ላይ በመንቀሳቀስ የጥቃት አውታሮችን በማስተጓጎል እና የአየር ላይ የበላይነትን በማረጋገጥ እርስ በእርስ ተደጋግፈው ፍጹም የተሟላ የመከላከል አቅም ይፈጥራሉ።
የቅድመ-መከላከል ዋና ፍልስፍና “ጦርነትን መፈለግ ሳይሆን፣ ጦርነት እንዳይከሰት ማድረግ” ነው። ቴክኖሎጂው የተሟላለት ዝግጁ የሆነ እና በሰለጠነ የሰው ኃይል የተደገፈ መከላከያ ሠራዊት ሲኖር የሀገራችን የውጭ ፖሊሲና ሰላም የማስከበር ጥረቶች በጠንካራ ምሰሶ ላይ ይቆማሉ።
የኢትዮጵያ ሰማይ በኤስ-400 እና በሱ-35 ጥበቃ ስር መዋሉ የአየር ክልላችንን ፍጹም ነፃነት የሚያረጋግጥ ሲሆን ማንኛውም አካል የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እና ሉዓላዊነት ለመድፈር ሲያስብ የወታደራዊ አቅሟን ከብቃት አንጻር መገምገም ግዴታ ያደርገዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ አቅም ማደግ በቀይ ባሕር፣ በአፍሪካ ቀንድ እና በምሥራቅ አፍሪካ ጂኦፖለቲካዊ መልክዓ ምድር ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል።
ቀጣናው በተለያዩ የጸጥታ ችግሮች እና ውጫዊ ኃይሎች ፉክክር የሚታመስበት በመሆኑ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የመከላከል አቅም በቀጣናው የሰላም መልህቅ በመሆን ያልተረጋጉ አካባቢዎች ወደ ሰላም እንዲመጡ ሚዛን የመጠበቅ ሚና ይኖራታል።
“ጠንካራ ወታደራዊ አቅም የጠንካራ ዲፕሎማሲ መሠረት ነው” እንዲሉ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የደኅንነት ጉዳዮች ላይ ስትደራደር ድምጿ ክብደት እንዲኖረው ይህ አዲስ የመከላከያ አቅም ከፍተኛ የዲፕሎማሲያዊ መተማመን ይሰጣታል።
የኢትዮጵያ በSu-35 ተዋጊ ጄቶች እና በS-400 የአየር መከላከያ ሥርዓቶች መታጠቅ የሀገራችንን የረጅም ጊዜ የሰላም እና የልማት ራዕይ ከሚያረጋግጡ ታላላቅ እርምጃዎች አንዱ ነው። ይህ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሀገራችን ታሪካዊ ሉዓላዊነቷን በአስተማማኝ ሁኔታ እንድትጠብቅ በቀጣናው ሰላም እንዲሰፍን የድርሻዋን እንድትወጣ እና በማንኛውም የውጭ ጫና የማይናወጥ ብሔራዊ አቋም እንድትይዝ ያስችላታል።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: