Search

የኢትዮጵያ፣ የብሪክስ እና የቻይና የቤልት ኤንድ ሮድ አጋርነት የተከፈተው አዲስ መንገድ

ሰኞ ጥቅምት 23, 2019 47

ኢትዮጵያ በጥንታዊ ሥልጣኔዎቿና በነፃነት ታሪኳ ለአህጉረ አፍሪካና ለደቡቡ ዓለም ድምፅ ሆና የኖረች ሀገር እንደመሆኗ ዛሬም በ21ኛው ክፍለ ዘመን አዲስ የጂኦፖለቲካ ሚዛን ውስጥ ማዕከላዊ የውሳኔ ሰጪነት ሚናዋን በከፍተኛ ድምቀት እየተወጣች ትገኛለች።

የቻይናው የቤልት ኤንድ ሮድ (BRI) ዘመናዊ የመሠረተ ልማት ግንባታ እና የብሪክስ ስብስብ መስፋፋት የቆየውን የብሬተን ውድስ የፋይናንስ ሥርዓት በለወጡበት በዚህ ወሳኝ ወቅት፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና (AfCFTA) መሪ እና የብሪክስ አባል በመሆን የደቡቡን ዓለም የልማት አቅጣጫ በብቃት በመቅረጽ ላይ መሆኗ የዘመኑ ታላቅ እውነት ነው።

በ2013 ዓ.ም የተወጠነው የቻይና የቤልት ኤንድ ሮድ ፕሮጀክት ከአህጉረ አፍሪካ ጋር በሚያደርገው ዘመናዊ የንግድና የመሠረተ ልማት ትስስር ውስጥ ኢትዮጵያ ልዩና ማዕከላዊ ቦታ ይዛለች።

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ኢትዮጵያ የምስራቅ እስያ የኢንዱስትሪ እድገት ሞዴልን በራስ አቅም ለመድገም የምትችል የተግባር ተምሳሌትና በቤልት ኤንድ ሮድ እና በአፍሪካ ልማት መካከል የምትገኝ ዋና ድልድይ ሆና ተገኝታለች።

የ752 ኪሎ ሜትሩ የአዲስ አበባ-ጅቡቲ የኤሌክትሪክ ባቡር መስመር ኢትዮጵያ የወጪ ንግዷን 90 በመቶ የሚያንቀሳቅስበትና የባሕር በር እጥረት ተግዳሮቷን የፈታበት ታሪካዊ ፕሮጀክት ነው።

ከዚህ ጎን ለጎን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ፣ የቴሌኮም መሠረተ ልማት መስፋፋት እና በቅርቡ የተጀመረው የሀገር ውስጥ የተፈጥሮ ጋዝ ልማትና የአንበሳ አውቶብሶች የኢነርጂ ሽግግር፤ ኢትዮጵያ የውጭ ፋይናንስን ከራሷ ሀገራዊ ፍላጎት ጋር አጣጥማ የመጠቀም አቅሟን እና ለአህጉሪቱ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ሞዴልነቷን ያረጋገጠችበት አዲስ የሥልጣኔ ምዕራፍ ነው።

ዛሬ ኢትዮጵያ የብሪክስ ሙሉ አባል በመሆኗ እና ከቻይና ልማት ባንክ እንዲሁም ከኒው ዲቨሎፕመንት ባንክ (NDB) ጋር በፈጠረችው ጠንካራ ትስስር ያለ ርዕዮተ-ዓለማዊ ጫና እና ሉዓላዊነትን ባከበረ መልኩ ለኢንዱስትሪና መሠረተ ልማት የሚሆን የፋይናንስ አማራጭ ማግኘት ችላለች።

ኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና አጋሮቻቸው በብሪክስ መድረክ ያገኙት ድምፅ አፍሪካውያን ከዓለም አቀፍ ውሳኔ ጠባቂነት ወደ ሕግ አውጪነትና መሪነት እንዲሸጋገሩ ያስቻላቸው ሲሆን ይህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ እና የኢኮኖሚ ድርድር ላይ ያላትን የድርድር አቅም ከፍ አድርጎታል።

እናም ታሪክ እንደ ወንዝ ፈሳሽ እንደመሆኑ መጠን ታሪክን ማውራት ብቻ ሳይሆን ታሪክን በመሥራት የዛሬን እውነትና የነገን ብሩህ ተስፋ መቅረጽ እንደሚገባ የመደመር ፍልስፍና ያስገነዘባል።

ኢትዮጵያ ከአክሱም እና ላሊበላ የነበራትን ጥንታዊ የሥልጣኔ መሠረት፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በወጣት የሰው ኃይሏ በተፈጥሮ ሀብቷ፣ በአህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና መሪነቷ እና በዘመናዊ መሠረተ ልማቶቿ አድሳ እየተነሳች ትገኛለች።

ከውጭ የተቀዱ ርዕዮተ-ዓለሞችን በመተው በሀገር በቀል እሳቤና በትጋት መሥራት፣ ጥሬ ሀብትን በሀገር ውስጥ በማቀናበር እሴት መጨመር እና የዓለም አቀፍ የኃይል ሚዛኑን ለሕዝብ ጥቅም ማዋል የዚሁ የሥልጣኔ ጉዞ ማረጋገጫ ናቸው።

ኢትዮጵያ በተባበረ ክንድ፣ በዕውቀትና በሀብት በመደመር የቀደመ ገናናነቷንና ታላቅነቷን በጸና መሠረት ላይ ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሰራች የምትገኘውም ለዚሁ ነው።

በሰለሞን ገዳ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: