Search

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ፡ እስከ ዓለም አቀፍ መድረክ መሪነት የዘለቀ አርዓያነት

ሰኞ ጥቅምት 23, 2019 40

የኢትዮጵያ የጸና የዲፕሎማሲ መርህ እና መዋቅራዊ አቋም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያጋጥሟትን የጂኦፖለቲካዊና የኢኮኖሚ ፈተናዎች በብቃት እንድትወጣ የሚያስችላት ቁልፍ መሳሪያ ሆኗል።

ይህ ስትራቴጂያዊ አካሄድ ኢትዮጵያ በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን ግንኙነቶቿ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ተደማጭነቷና ተቀባይነቷ በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ አድርጓል።

የኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ እና የዲፕሎማሲ መሠረት የዓለም አቀፍ ሕጎችን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተርን እና የአፍሪካ ሕብረት መሠረታዊ መርሆዎችን በሙሉ ልብ ማክበርና መደገፍ ነው።

ኢትዮጵያ የሀገራትን እኩልነት የምታከብር እና የምታስቀድም እንዲሁም ማንኛውንም አለመግባባት በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ የመፍታት መርህን የምትከተል ናት። ይህም በቀጣናው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ አስተማማኝና ኃላፊነት የሚሰማት ሀገር እንድትሆን አድርጓታል።

ከእነዚህ ታላላቅ የዲፕሎማሲ ስኬቶች መካከል ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2027 የሚካሄደውን 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) በአዲስ አበባ እንድታስተናግድ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሙሉ ይሁንታ መመረጧ ዋነኛው ማሳያ ነው።

ይህ ውሳኔ በዘፈቀደ የተሰጠ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በአጭር ጊዜ ውስጥ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ያሳየችውን ተጨባጭ ተግባር፣ የታዳሽ ኃይል ልማቷን እና ለአየር ንብረት ጽናት የምታደርገውን አህጉራዊ አስተዋጽኦ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሰጠው ትልቅ እውቅና ነው።

ጉባኤው የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ መካሄዱ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለበረታባት አፍሪካ የተግባር እና የመፍትሔ ማሳያ እንድትሆን ያስችላታል።

ሀገራችን ከቃል ባለፈ በተግባር የጸናች የአረንጓዴ ልማት አርዓያ መሆኗን በማረጋገጥም  የዓለም አቀፍ መድረኮችን ለመምራት የሚያስችላትን አቅም አግኝታለች።

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ መርህ ዓለም አቀፍ ሕጎችን በማክበር፣ የጋራ ተጠቃሚነትን በማስቀደም እና እንደ ኮፕ 32 ያሉ ታላላቅ ዓለም አቀፍ መድረኮችን በበላይነት በመምራት የኢትዮጵያ የጂኦፖለቲካዊ ቁመና እና ተደማጭነት በአዲሱ የዓለም አቀፍ ምዕራፍ ከፍ እያደረገ ይገኛል።

በሃና ምንዳሁን

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: