Search

ብዝኃነት እንደ ውበት፣ አንድነት እንደ ጥንካሬ፡- የመደመር እሳቤ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት

ሰኞ ጥቅምት 23, 2019 56

ኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት የታሪክ ጉዞዋ፣ የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ባህል፣ ቋንቋ፣ ቅርስና ማንነት የተሸመነችባት ባለብዙ ቀለም ሀገር ናት። ይህ የባህልና የታሪክ ሀብት ለሀገራችን ውበትና ዘላቂ ጥንካሬ እንጂ የልዩነት መሸርሸሪያ ሊሆን አይገባውም።

በቅርብ ዓመታት በስፋት እየተተገበረ ያለው "የመደመር እሳቤ" መሠረታዊ መርህም ይህንን እውነት ማዕከል ያደረገ እንዲሁም ብዝኃነትን ሳይደመስሱና ማንነትን ሳያጠፉ፣ ሁሉንም እኩል አክብሮ እና አልምቶ የጋራ አንድነትን መገንባት ላይ ያተኮረ ነው።

የአንድ ሀገር ዘላቂ አንድነት ሊረጋገጥ የሚችለው የሁሉም ሕዝቦች ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህል እና ቅርስ እኩል ክብርና ዕውቅና ሲያገኙ ብቻ ነው። የመደመር እሳቤ ታሪክን የጥልና የቁስል ምንጭ ከማድረግ ይልቅ፣ የሁሉንም አዎንታዊ አስተዋጽኦ በማቀናጀት የጋራ ትርክት መገንባት ላይ ትኩረት ያደርጋል።

የኦሮሞ የገዳ ሥርዓት፣ የትግራይ የአክሱም ሐውልት፣ የሲዳማ የፊቼ ጨምበላላ፣ የአፋር የሉሲ (ድንቅነሽ) ግኝት፣ የአማራ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የሐረሪ የጁገል ግንብና የሌሎችም ሕዝቦች እሴቶች የየአካባቢው ብቻ ሳይሆኑ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ሀብቶች ናቸው።

የሕዝቦችን ቋንቋና ባህል ማልማት የኢትዮጵያን የባህል ግምጃ ቤት የማበልጸጊያ መንገድ ነው። እያንዳንዱ ማንነት ሲከበርና ሲጎላ፣ ዜጎች በሀገራቸው ላይ ያላቸው የባለቤትነት ስሜትና ሀገራዊ ፍቅር ይበልጥ ይጠናከራል።

የሀገራችንን ባህላዊና ታሪካዊ ሀብቶች በእኩልነት ማልማት እና ማስተዋወቅ ለማኅበራዊ ትሥሥር ብቻ ሳይሆን ለኢኮኖሚ ዕድገትም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።

በቱሪዝም ዘርፍ የኮሪደር ልማት፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ የገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የቱሪስት ፍሰትን በማሳደግ፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማበልጸግና የሀገር ምሥልን በመገንባት ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።

የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶች፣ የባህል ሳምንታት እና የሀገራዊ በዓላት በጋራ ማክበር የእርስ በእርስ ግንዛቤን ማሳደግ፣ ጥላቻን ማስወገድና ማኅበራዊ ወንድማማችነትን በማጽናት ማኅበራዊ ትሥሥርን በማጉላት ሀገራዊ አንድነትን እያጠናከረ ነው።

የመደመር እሳቤ ዋና መርህ አዎንታዊ እሴቶችን አቀናጅቶ አዲስ እና ጠንካራ ኃይል መፍጠር ነው። ብዝኃነት እና አንድነት የኢትዮጵያ ሁለት መሠረታዊ ክንፎች ናቸው። ብዝኃነት ከሌለ አንድነት ጭቆና እና ጭፍለቃ ይሆናል፤ አንድነት ከሌለ ደግሞ ብዝኃነት ወደ መበታተን ያመራል።

የመደመር እሳቤ ሁለቱን አጣጥሞና አስተሳስሮ ያስኬዳል። ያለፉ ታሪካዊ እውነታዎችን በበጎ በመተርጎም፣ ለትውልድ የሚጠቅሙ የጋራ እሴቶችን ማስቀደም የመደመር መሠረታዊ አስተሳሰብ ነው።

ኢትዮጵያ የብዙ ሕብረ ቀለማት ሀገር ናት። የሕዝቦቿ ብዝኃነት የተፈጥሮ ሀብቷ፣ የባህሏ ውበት እና የጋራ ጥንካሬዋ እንጂ የስጋት ምንጭ አይደለም። በሁሉም አቅጣጫ የሚገኙ ሕዝቦችን ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህልና ቅርስ በእኩልነት ማልማትና ለትውልድ ማስተላለፍ የጽኑ ሀገራዊ አንድነት መሠረት ነው።

የመደመር እሳቤ ይህንን እውነት በተግባር በማረጋገጥ፣ ብዝኃነትን ጠብቆ የጋራ ቤታችንን ኢትዮጵያ በጠንካራ መሠረት ላይ የመገንባት መንገድን ያሳያል። እያንዳንዱ ማንነት ሲከበርና ሲበለጽግ ሀገራችን በዚያው ልክ ትገዝፋለች፣ ዘላቂ ልማትና ሰላሟም በጥንካሬ ይረጋገጣል።

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: