አፍሪካ በጤናው ዘርፍ ከውጭ ጥገኝነት ራስን ወደ መቻል እንዲሁም ከተጋላጭነት ወደ ጠንካራ የመቋቋም አቅም ለማሸጋገር ያለመው እና በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው አህጉራዊ ጉባኤን በስኬት ለማጠናቀቅ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ከኅዳር 14 እስከ 18 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ ለሚካሄደው የአፍሪካ የሕብረተሰብ ጤና ጉባኤን አስመልክቶ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዣን ካሴያ ዛሬ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ በአህጉራዊው ጉባኤው 54ቱ የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት ተወካዮችን ጨምሮ ከ114 ሀገራት ከ30 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች በአካልና በበይነ-መረብ ይሰተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከእነዚህም መካከል ከ4 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ ተሳታፊዎች መመዝገባቸውን ገልጸው፣ በጉባኤው ከ6 ሺህ በላይ ሳይንሳዊ ጥናቶች ለመቅረብ መዘጋጀታቸውን እንዲሁም የኤግዚቢሽን እና የመስክ ልምድ ልውውጥ መርሐ ግብሮች መኖሩን ተናግረዋል።
ጉባኤው በጤናው ዘርፍ የተመዘገቡ የፖሊሲና የመሠረተ ልማት ለውጦችን ለማሳየት፣ ሳይንሳዊ ምርምሮችን ለመገምገም እንዲሁም አፍሪካ በመድኃኒት አቅርቦትና በዲጂታል ጤና ራስን ለመቻል እያደረገች ያለችውን ጥረት ለማሳየት የሚረዳ ትልቅ መድረክ ነው ብለዋል።
ዶክተር ዣን ካሴያ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እያከናወነች ያለውን ስርነቀል ሥራ ለመገንዘብ በአዲስ አበባ እየተገነባ ያለውን የጤና መረጃ ማዕከል (Health Intelligence Center) መመልከት በቂ ነው ብለዋል።
ማዕከሉ በአፍሪካ ካዩዋቸው እጅግ ዘመናዊና አስደናቂ የጤና ማዕከላት አንዱ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህም የኢትዮጵያን የጤና ዘርፍ ዘመናዊነትና የአፍሪካ አህጉራዊ ተሳትፎ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
አፍሪካ የራሷን የጤና ችግሮች በራሷ የመፍታት አቅም መገንባት፣ የምርምርና የሕክምና ምርቶች ማምረት አቅሟን ማሳደግ እንዲሁም የጤና ሥርዓቷን ማጠናከር እንደሚጠበቅባት ገልጸው፣ ጉባኤውን በጥራት ለማስተናገድ ለተደረገው ዝግጅት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ለጤና ሚኒስትሯ ምስጋና አቅርበዋል።
ጉባኤው የአፍሪካ ዜጎች በጤናው ዘርፍ ከውጭ እርዳታና ጥገኝነት በመላቀቅ፣ በራሳቸው አቅም፣ ሀብትና የምርምር አቅም ላይ የተመሠረተ ዘላቂ መፍትሔ ለመቀየስ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ተብሏል።
ኢትዮጵያ ይህንን ታሪካዊ ስብሰባ ማስተናገዷ ከዲፕሎማሲያዊ ማዕከልነቷ ባሻገር፣ በአፍሪካ የጤና ፖሊሲ፣ በሳይንሳዊ ምርምር እና በአህጉራዊ ቅንጅት ያላትን መሪ ሚና ይበልጥ የሚያጠናክር ይሆናል።
ከሦስት ሳምንታት በኋላ ለሦስት ቀናት በሚቆየው በዚህ አህጉራዊ ጉባኤ፣ ከአፍሪካ እና ከመላው ዓለም የተሰበሰቡ መሪዎች፣ ሳይንቲስቶች፣ ፈጣሪዎች፣ ወጣት ባለሙያዎች እና የለውጥ አራማጆች በአዲስ አበባ ተሰብስበው ስለ አፍሪካ የጤና ደህንነት እና ሉአላዊነት በሚደረገው ታሪካዊ ውይይት ላይ ይመክራሉ።
በመሃሪ ዓለሙ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: