በአዲስ አበባ የህፃናት ሙዚየም ለማቋቋም ኢትዮጵያ እና ቼክ ሪፐብሊክ ስምምነት ተፈራረሙ።
የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ከቼክ ብሔራዊ ሙዚየም እና ከቼክ ዲቨሎፕመንት ኤጀንሲ ኃላፊዎች ጋር ስምምነቱን በፕራግ ከተማ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ህፃናትን ማዕከል ያደረገ ዘመናዊ ሙዚየም መገንባት የሚያስችል ሲሆን፤ የቼክ ሪፐብሊክ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግ ይሆናል።
ይህ ቋሚ የልጆች ሙዚየም በወዳጅነት ቁጥር 2 ፓርክ ውስጥ የሚገነባ እንደሆነም ተገልጿል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፥ የህፃናት ሙዚየሙ ህፃናት ቀለል ባለ መንገድ ስለ ሀገራችን ታሪክ እና ባህል እውቀት እንዲኖራቸው ከማስቻሉም በላይ በፈጠራ፣ በትምህርትና በእውቀት እንዲጎለብቱ እድል የሚፈጥርላቸው መሆኑን ገልፀዋል።
የቼክ መንግስት ይህንን ሙዚየም ለማቋቋም ለሚያደርገው የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።
ይህ ቋሚ የህፃናት ሙዚየም ፕሮጀክት ህፃናት የቱሪዝም ሀብቶቻችንን አውቀው እንዲያድጉ እና በዘርፉ ልማት ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ የሚያግዝ እንደሆነም ተገልጿል።
በመቅደላዊት ደረጀ