ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት እና የሉዓላዊነት ምልክት ሆና በጽናት በመዝለቅ ከዘመናዊው ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ሥርዓት ጋር በጥልቀት ተሳስራ ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን አስቀጥላለች።
በአውሮፓ የቅኝ ግዛት ማዕበል መካከል በዓድዋ ድል ነፃነቷን በማስከበር ለዓለም አቀፍ ሕግና ለጋራ ደኅንነት የነበራትን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይታለች።
ይህ ጽናቷም እ.አ.አ በ1923 የሊግ ኦፍ ኔሽንስ አባል እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቀዳሚ መሥራች በመሆን መላው አፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረክ ድምፅ እንዲኖራት አስችሏል።
የሕዝቦች እኩልነት መርሕ እና የነፃነት ተምሳሌትነቷ አዲስ አበባን የአፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) ዋና መቀመጫ በማድረግ የአህጉሪቱ ዲፕሎማሲያዊ መዲና አድርጓታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ እንዳረጋገጡት የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከዘመን ዘመን የማይለወጠውን የነፃነት፣ የእኩልነት እና የፍትሐዊነት መርሕ መሠረት ያደረገ ነው።
"ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ" የሚለው ጽኑ አቋሟ እና አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ የሚሆንበትን የቆየ አካሄድ በማስቀረት የጋራ አሸናፊነትን መከተሏ ለዲፕሎማሲያዊ ስኬቶቿ ዋነኛ ምሰሶ ሆኗል።
ዛሬም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች፣ ሽብርተኝነትን በመዋጋት፣ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እና በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ድርድሮች ለአፍሪካ ድምፅ በመሆን ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች ትገኛለች።
ከዚህ ጎን ለጎን የብሪክስ (BRICS) አባል መሆኗ ጂኦስትራቴጂያዊ ሚዛኗን፣ ዓለም አቀፋዊ ተሰሚነቷን እና የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነቷን ይበልጥ እያጎለበተው ነው።
ሥልታዊ ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ያለ ጦርነት እና ግጭት ከማስጠበቁም ባሻገር ውጤታማ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን በመከተል የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ አዳዲስ የንግድ ገበያዎችን ለመክፈት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠን ትልቅ ድርሻ አበርክቷል።
በመደመር መንግሥት የውጭ ግንኙነት መርህ "ቅድሚያ ለጎረቤት" የሚለው አቅጣጫ ተግባራዊ በመሆኑ፣ ድንበር ተሻጋሪ የልማት ሥራዎች እና የመሠረተ ልማት ትስስሮች ቀጣናዊ ሰላምን እና የጋራ ብልጽግናን እውን እያደረጉ ይገኛሉ።
ለዚህም በሳይንሳዊ እውነታዎች እና በጋራ ልማት ላይ የጸና የዲፕሎማሲ ድል የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምሥራቅ አፍሪካን በኃይል አቅርቦት እያስተሳሰረ መሆኑ ሕያው ማሳያ ነው።
ከዚህም ባሻገር የዘመናዊው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ትልቁ መለያ ዜጋ ተኮር መሆኑ ነው። ይህም በተለያዩ ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በክብር ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዳያስፖራዎች በሰላም ግንባታ እና በልማት ሥራዎች ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
የዲፕሎማሲያችን ዋነኛ ጉልበት ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ነው።
የብሔር፣ የቋንቋ እና የሃይማኖት ልዩነቶቻችንን እንደ ጌጥ በመያዝ ውስጣዊ ሰላማችንን እና ዴሞክራሲያችንን ባጠናከርን ቁጥር ማንኛውንም የውጭ ጫና በመመከት በዓለም አደባባይ ቀና ብለን መቆም እንችላለን።
በጋራ ልማት፣ በፍትሐዊ የሀብት አጠቃቀም እና በዜጎች ክብር ላይ የተመሠረተው ይህ የዲፕሎማሲ ጉዞ ኢትዮጵያን ወደ ተሟላ ልዕልናዋ እንደሚያሸጋግራት አያጠራጥርም።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: