በመቐለ ከተማ በሚከናወነው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ዙሪያ ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ከተውጣጡ ምሁራን፣ ተመራማሪዎች እና የዩኒቨርሲቲው አመራር አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል።
ውይይቱ የከተማዋን ነባራዊ ገጽታ ማሻሻል፣ የዕድገት ፍጥነቷን ማሳደግ እና ለነዋሪዎች ምቹ የሆነ ዘመናዊ መሠረተ ልማት እውን ማድረግ በሚያስችሉ ሐሳቦች ላይ ያተኮረ ነው።
በውይይቱ ወቅት የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቱ ከከተማ ፕላን፣ ከማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲሁም ከዘላቂ የከተማ አስተዳደር አንጻር ሰፊ ትንተና ተሰጥቶበታል።
ምሁራኑ በሰጡት አስተያየት፣ የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ውበት ከመጠበቁም በላይ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለማቀላጠፍ፣ የትራፊክ ፍሰትን ለማሻሻል እና የዜጎችን የኑሮ ጥራት ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
ሆኖም ፕሮጀክቱ ስኬታማ እንዲሆን ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለው ቅንጅት መጠናከር እንዳለበት፣ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ በተለይም የባለቤትነት መንፈስ ማሳደግ ላይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።
የዩኒቨርሲቲው ምሁራን በከተማ ልማት፣ በኢንጂነሪንግ፣ በሥነ-ምህዳር እና በማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፎች ያላቸውን ዕውቀትና ምርምር በመጠቀም ለፕሮጀክቱ ስኬት ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የከተማ አስተዳደሩ እና የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች በበኩላቸው፣ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን የሚያነሷቸው ሳይንሳዊ አስተያየቶችና ግብዓቶች ለዕቅድ ማሻሻያ እና ለአፈጻጸም ጥራት እጅግ ጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፣ ወደፊትም አብሮነቱ እንደሚዘልቅ አስታውቀዋል።
በአስማረ ብርሃኑ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: