Search

የኢትዮጵያን ምርት እና አገልግሎት ለአሜሪካዊያን እና የቢዝነስ ማኅበረሰብ ለማስተዋወቅ ያለመ የቡና ፌስቲቫል ተካሄደ

ማክሰኞ ኅዳር 08, 2019 129

የኢትዮጵያን ቡና የሚያስተዋውቅ “Taste of Ethiopian Coffee” የተባለ ፌስቲቫል ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የአሜሪካ ዜጎች እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት በድምቀት ተካሂዷል።

ፌስቲቫሉ የኢትዮጵያን ምርት እና አገልግሎት ለአሜሪካዊያን ዜጎች እና የቢዝነስ ማኅበረሰብ የማስተዋወቅ እና የገበያ ትሥሥር ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

በፌስቲቫሉ ላይ ከ300 በላይ ተሳታፊዎች ከኢትዮ-አሜሪካ ንግድ ምክር ቤት፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ አሜሪካውያን ዜጎች፣ DMV አካባቢ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት፣ የሚዲያ ባለሙያዎች፣ የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች እንዲሁም የተለያዩ ምርቶችና አገልግሎቶችን የሚያስተዋውቁ የቢዝነስ ተቋማት ተሳትፈዋል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ብናልፍ አንዱዓለም በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ቡና ለኢትዮጵያዊያን የዕለት-ተዕለት ኑሮ አንስቶ በማኅበራዊ ግንኙነት ያለውን ጥብቅ ቁርኝት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ቡና ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ያለውን ፋይዳ እና ከሌሎች ሀገራት ቡና ጋር ሲነፃፀር ያሉትን ልዩ የጣዕምና የጥራት ተምሳሌትነት ለታዳሚዎች አስረድተዋል።

ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሚኖሩበት አካባቢ ባላቸው የንግድ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን ባህል፣ ምርት እና አገልግሎት ለሌሎች ሀገራት ማስተዋወቅ ሁሉም ለሀገሩ አምባሳደር መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ በመግለፅ፣ በቀጣይም የትውልድ ሀገራቸውን ምርትና አገልግሎቶች ለአሜሪካውያን በስፋት በማስተዋወቅ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በመጨረሻም ከኤምባሲው ጋር በመተባበር ፕሮግራሙን ላዘጋጁት አካላት እና ለፕሮግራሙ መሳካት አስተዋፅኦ ላደረጉ ተቋማትና ግለሰቦች እንዲሁም ለታዳሚው ምስጋና ማቅረባቸው በዋሽንግተን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: