የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ከ3 ሺህ ዓመታት በላይ የሚሻገር ጥልቅ ታሪክ ያለው፣ በጥንታዊ የሥነ ሕንጻ፣ የድንጋይ ፍልፍል እና የምህንድስና ጥበብ የዓለምን ትኩረት የሳበ ነው።
ከአንድ ወጥ ድንጋይ ተፈልፍለው የተሠሩት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የአክሱም ሐውልት እንዲሁም የሶፍ ዑመር ዋሻ ኢትዮጵያውያን ከድንጋይ እና ከተፈጥሮ ጋር ያላቸውን የቆየ ብልሃት እና ጥበብ ያሳያሉ።
የመደመር መንግሥት ይህንን ታሪካዊ የፈጠራ እና የምህንድስና እሴት እንደ መነሻ በመጠቀም የሀገር በቀል ዕውቀትን እና ነባር ወረቶችን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር የከተማ ልማትን በአዲስ መንገድ እያከናወነ ይገኛል።
በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ያሉት የኮሪደር ልማቶች እና በተለያዩ የመዲናዋ ፓርኮች የሚስተዋሉት ሰው ሠራሽ ዋሻዎች፣ ፏፏቴዎች እና የድንጋይ ቅርጻ ቅርጾች የጥንቱን ሥነ-ጥበብ በዘመናዊ መልክ ያንጸባርቁ ሥራዎች ናቸው።
ዛሬ ላይ መሐንዲሶች፣ አርክቴክቶች እና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ቴክኖሎጂ በመጠቀም ተፈጥሯዊ ገደሎች እና ዋሻዎችን የሚመስሉ ውብ ሥፍራዎችን በመዲናዋ እየፈጠሩ ይገኛሉ።
በልዩ የኮንክሪት ውህድ እና በተፈጥሮ ቀለማት ቅብ የሚዘጋጁት እነዚህ ዋሻዎች እና ፏፏቴዎች፣ የከተማዋን ውበት እና ማራኪነት በእጅጉ አሳድገዋል።
ባለፉት ስምንት ዓመታት የታየው ለውጥ ከውጭ የተቀዱ ንድፎችን ብቻ ከመውሰድ ይልቅ፣ የኢትዮጵያን ታሪካዊ አሻራ እና የማንነት ቅርጽ የያዙ ዘመናዊ መሠረተ ልማቶችን መገንባት መቻሉን ያሳያል።
የላሊበላ ባለሙያዎች ድንጋዩን ፈልፍለው ከተፈጥሮ ጋር የተዋሐደ ቅርስ እንዳቆዩ ሁሉ፣ የዛሬው ትውልድም ያንን የፈጠራ መንፈስ በመውረስ ከተማን ከተፈጥሮ ጋር የሚያስተሳስሩ ሥራዎችን እያከናወነ ነው።
በአዲስ አበባ የተገነቡት ሰው ሠራሽ ዋሻዎች እና ፏፏቴዎች ለዕይታ ማራኪ ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ ለተለያዩ እንስሳት እና አእዋፋት ምቹ መጠለያ በመሆን የከተማዋን ሥነ-ምኅዳር ይደግፋሉ።
እንዲሁም ለነዋሪዎች እና ለጎብኚዎች የመንፈስ እርካታ፣ የማኅበራዊ መስተጋብር እና የመዝናኛ ሥፍራ ሆነው በማገልገል የከተማዋን ሕይወት አድምቀዋል።
ትላንት አክሱምን እና ላሊበላን የገነቡት የኢትዮጵያውያን ጠቢባን እጆች ዛሬም ሳይቋረጡ በዘመናዊ የምህንድስና እና የፈጠራ ሥራዎች እየቀጠሉ ነው።
የመደመር መንግሥት ለሀገር በቀል ዕውቀት፣ ለፈጠራ እና ለኪነ ጥበብ የሰጠው ትኩረትም ኢትዮጵያ የሺህ ዓመታት የሥልጣኔ መንገዷን ጠብቃ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ወደ ላቀ የብልጽግና ምዕራፍ እየተሸጋገረች መሆኗን አረጋግጧል።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: