Search

ጅማ፡ ከጥንታዊ የከተማ ንድፍና ቅርስ እስከ ብሔራዊ የአንድነት መድረክ

ዓርብ ኅዳር 11, 2019 101

ጅማ በታሪክ፣ በባህል እና በተፈጥሮ ጸጋ የበለጸገች፣ የኢትዮጵያን ብዝኃነት እና አንድነት የምታንጸባርቅ ታላቅ ከተማ ናት።

ከተማዋ በ1931 ዓ.ም በተዘጋጁ የከተማ ፕላን እና የሕንፃ ንድፍ ዕቅዶች ውስጥ ከተካተቱ ቀዳሚ ስፍራዎች አንዷ ስትሆን፣ ዛሬ ደግሞ በመንግሥት እና በሕዝብ የተቀናጀ ተሳትፎ በተከናወኑ የኮሪደር እና የመሠረተ ልማት ሥራዎች አዲስ ገጽታ ተላብሳለች።

የጅማ የእንግዳ ተቀባይነት መገለጫ ከሆኑት ነገሮች መካከል በጀበና ተፈልቶ በበርካታ ሲኒዎች የሚቀርበው የቡና ሥነ-ሥርዓት ይጠቀሳል።

የቡና መዓዛ እና የአቀራረብ ሥርዓት ከአካባቢው ማኅበራዊ ሕይወት ጋር የተሳሰረ ሲሆን፣ ለእንግዶች የሚሰጠው ክብር የከተማዋን ልዩ መስህብ ይበልጥ ያጎላል።

ከዚህ ባሻገር ከ130 ዓመት በላይ ዕድሜ ያለው ታሪካዊው የአባ ጅፋር ቤተ መንግሥት የጥበብ እና የታሪክ ዐሻራ ሆኖ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኚዎችን ትኩረት ይስባል።

ጅማ በዓመት አብዛኛውን ወራት ዝናብ የምታገኝ ለምለም እና አረንጓዴ ምድር ናት፡፡ ይህ የተፈጥሮ ጸጋ በባህላዊ አልባሳት ላይ በሚታየው አረንጓዴ ቀለም ጭምር ይንጸባረቃል፤ ቀለሙም የለምለምነት፣ የተስፋ እና የብልጽግና ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል።

ይህንን ታሪካዊ እና ባህላዊ ሀብት የያዘችው ጅማ፣ ኅዳር 29 የሚከበረውን 21ኛውን የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቅቃ እንግዶቿን እየጠበቀች ነው።

ባለፈው ዓመት ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተረከበችውን የአንድነት ሰንደቅ ቃል በተግባር ለማክበር እና የኢትዮጵያን ብዝኃነት የሚያደምቅ መድረክ ለመፍጠር ጅማ ሁሉንም ሕዝቦች እና እንግዶችን በፍቅር ለመቀበል ዝግጁ ሆናለች።

በልዩ እሸቱ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: