የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2019 በጀት ዓመት ባለፉት አራት ወራት ብቻ 2 ሺህ 472 ኪ.ሜ የኤሌክትሪክ መስመሮችን የመልሶ ግንባታ፣ የማሻሻያ እና የማስፋፊያ ሥራ ማከናወኑን አስታወቀ።
ሥራዎቹ በተቋሙ የውስጥ ፋይናንስ ብቻ የተከናወኑ መሆናቸውን የአገልግሎቱ ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አንዋር አብራር ለኢቢሲ ዶትስትሪም ገልጸዋል።
በዚህም በነባር መስመሮች ላይ በተከናወነው የመልሶ ግንባታና የማሻሻያ ሥራ 749 ኪ.ሜ መካከለኛ መስመር እና 82 ኪ.ሜ ዝቅተኛ መስመር በድምሩ 831 ኪ.ሜ ሥራ ተከናውኗል ብለዋል።
በተጨማሪም ከአቅማቸው በላይ በጭነት ምክንያት የአገልግሎት መቆራረጥ ሊያስከትሉ የሚችሉ 481 ትራንስፎርመሮች በከፍተኛ አቅም ባላቸው ትራንስፎርመሮች መተካታቸውን ገልጸው፣ 411 ተጨማሪ ትራንስፎርመሮች በተለያዩ አካባቢዎች ተከላ ተደርጎላቸዋልም ያሉት።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሽፋንን ለማስፋፋት በተከናወነው ሥራ ደግሞ 978 ኪ.ሜ መካከለኛ መስመር እና 662 ኪ.ሜ ዝቅተኛ መስመር በድምሩ 1 ሺህ 641 ኪ.ሜ አዲስ መስመር መዘርጋቱንና በእነዚህ የማስፋፊያ ሥራዎች 1 ሺህ 744 ትራንስፎርመሮች ተከላ እንደተደረገላቸው አመልክተዋል።
እነዚህ ሥራዎች በተቋሙ የውስጥ ፋይናንስ ብቻ መከናወናቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የነባር መስመሮችን ጥራትና አቅም ለማሻሻል፣ የኤሌክትሪክ ሽፋንን ለማስፋፋት እና የአገልግሎት ተደራሽነትንና ቀጣይነትን ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
የመስመሮች መልሶ ግንባታና ማሻሻያ፣ የትራንስፎርመሮች አቅም ማሳደግ እና አዳዲስ መስመሮችን መዘርጋት የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለማጠናከር፣ የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻልና የኢንዱስትሪ፣ የንግድ፣ የግብርና እና የማኅበራዊ አገልግሎቶች ዕድገትን ለመደገፍ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ጠቁመዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: