Search

የ'ስቶፕ-ኦቨር' (Stopover Tourism) ቱሪዝም ማዕከል እየሆነች ያለችው አዲስ አበባ

ረቡዕ ኅዳር 09, 2019 143

የእግረ መንገድ ቱሪዝም (Stopover Tourism) ተጓዦች ከመነሻቸው ተነስተው ወደ ሌላ መዳረሻ ሲበሩ በመሸጋገሪያ ሀገር ውስጥ ለጥቂት ሰዓታት ወይም ቀናት ቆይታ አድርገው የመሸጋገሪያውን ስፍራ መስህቦች እንዲጎበኙ የሚያስችል ዘመናዊ የቱሪዝም ዘርፍ ነው።

ይህ አሠራር የትራንዚት መንገደኞችን ወደ ቱሪስትነት በመቀየር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከማስገኘቱም ባለፈ፣ ተጓዦች በአጭር ቆይታቸው ስለ ኢትዮጵያ በቂ ግንዛቤ አግኝተውና ተማርከው ወደፊት ለረጅም ጊዜ ጉብኝት ተመልሰው እንዲመጡ መንገድ ይከፍታል። ለሀገር ገጽታ ግንባታ ያለው ፋይዳም እጅግ የጎላ ነው።

የብዝኃ ባህልና ታሪክ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ፣ በዚህ ዘርፍ ተጠቃሚ ለመሆን ሰፊ ዝግጅቶችን አድርጋ ወደ ተግባር ገብታለች።

በተለይም በአፍሪካ ግዙፉ የአየር ትራንስፖርት ማዕከል በሆነው ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል በየዓመቱ የሚያልፉትን ከ20 ሚሊዮን በላይ መንገደኞች ወደ ቱሪስትነት ለመቀየር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው።

አዲስ አበባም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ነባር መስህቦችን ከማደስ ባለፈ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን እና መሠረተ ልማቶችን ገንብታለች።

የአንድነት ፓርክ፣ የእንጦጦ ፓርክ፣ የወዳጅነት አደባባይ፣ የሳይንስ ሙዚየም እና የዓድዋ ድል መታሰቢያ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ሊጎበኙ የሚችሉ ምቹ መዳረሻዎች ሆነዋል።

ከመዳረሻዎቹ ግንባታ ጎን ለጎን በአዲስ አበባ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ለስቶፕ-ኦቨር ቱሪዝም ትልቅ አቅም ፈጥሯል።

ልማቱ ለትራንስፖርት መሳለጥና ለከተማዋ ውበት ካለው ፋይዳ ባለፈ፣ በምሽት የሚደምቁ ጎዳናዎችን፣ የእግረኛ መንገዶችን እና የመዝናኛ ስፍራዎችን በመፍጠር የምሽት ትራንዚት ላላቸው መንገደኞች ሳቢ አማራጭ ሆኗል።

ይህም በከተማዋ የጥቂት ሰዓታት ቆይታ የሚኖራቸው እንግዶች ደኅንነቱ በተጠበቀ እና ዘመናዊ በሆነ ከባቢ አዲስ አበባን እንዲጎበኙ ዕድል በመፍጠር የቱሪዝም ፍሰቱን እና ገቢውን በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል።

የአገልግሎት አሰጣጥን ከማዘመን አንጻርም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ8 እስከ 24 ሰዓት የትራንዚት ቆይታ ላላቸው መንገደኞች ነፃ የሆቴል መስተንግዶ፣ የትራንስፖርት እና የከተማ ጉብኝት ፓኬጆችን በማቅረብ ጎብኚዎችን እየሳበ ይገኛል።

በተጨማሪም የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተርሚናል መስፋፋት እንዲሁም የኢ-ቪዛ እና የትራንዚት ቪዛ አገልግሎት መቀላጠፉ፣ መንገደኞች አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የነበረውን የአገልግሎት መጓተት በማስቀረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ከተማ ወጥተው ሰፊ የጉብኝት ጊዜ እንዲኖራቸው አስችሏል።

በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ፣ ከተማን የማስዋብ እና የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎችን ከቱሪዝም ልማት ጋር በማስተሳሰር፣ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የትራንዚት ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የተያዙ ሀገራዊ ግቦች በተግባር እየተተረጎሙ ይገኛሉ።

ይህ የተቀናጀ ጥረት ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የቱሪዝም አቅም ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በመቀየር ረገድ ትልቅ ምዕራፍ ከፍቷል።

በዓይናለም ሃድራ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: