ነቀምቴ ከአዲስ አበባ በስተ ምዕራብ 328 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝና በ1830 ዓ.ም በደጃዝማች ሞሮዳ በከሬ የተቆረቆረች ጥንታዊ ከተማ ናት። በአሁኑ ወቅት እየተከናወነላት ባለው የኮሪደር ልማት ውበቷ ይበልጥ ጎልቶ፣ ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ምቹ እየሆነች ትገኛለች።
ከባሕር ጠለል በላይ 2 ሺህ 88 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘውና ደጋማ የአየር ንብረት ያላት ነቀምቴ፤ ከአዲስ አበባ፣ ከጅማ፣ ከአሶሳ እና ከባሕር ዳር ጋር በአራት መውጫና መግቢያ በሮች የምትገናኝ የምዕራብ ኦሮሚያ ዋነኛ የንግድና የእንቅስቃሴ መናኸሪያ ናት።
በኦሮሚያ ክልል ከተሞችን የፈጠራ፣ የኢንቨስትመንትና የብልጽግና ማዕከል ለማድረግ በተያዘው አዲስ የከተማ ልማት ዕሳቤ፣ ነቀምቴ በፈጣን የዕድገትና የለውጥ ጉዞ ላይ ትገኛለች።
በሰባት ክፍለ ከተሞች እና እንደ በኪጃማ፣ ቀሶ፣ ቦርድ፣ ሸዋበር፣ አጂፕ፣ ማርያም እና ደርጌ በሚባሉ ሰፈሮቿ የምትታወቀው ከተማዋ፣ በተፈጥሮ ሀብትና በሰው ኃይል ልማት የታደለች ታሪካዊ ስፍራ ነች። ነቀምቴና አካባቢው በእምነበረድ፣ በወርቅ እና በቡና ምርቱ እንዲሁም በገበያ ላይ በጥራቱ ተፈላጊ በሆነው የወለጋ ቅቤ በሰፊው ይታወቃሉ።
ነቀምቴና አካባቢዋ ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና ተፈጥሯዊ የቱሪዝም መስህቦችን አጣምረው የያዙ ናቸው። በ1881 ዓ.ም የተገነባው የንጉሥ ኩምሳ ሞሮዳ ቤተ-መንግሥት፣ የወለጋ ባህልና ታሪክ ሙዚየም፣ ጥንታዊቷ የማርያም ቤተ ክርስቲያን እና ታሪካዊ የድንጋይ ፍልፍል ዋሻዎች የአካባቢውን የዳበረ ታሪክ የሚዘክሩ ቅርሶች ናቸው።
በተፈጥሮ መስህብነትም የሶርጋ ሰው ሠራሽ ሐይቅ፣ የሶር ፏፏቴ፣ ብርቅዬ የዱር እንስሳትና አዕዋፋት የበለጸገው የዲዴሳ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ፣ ጥቅጥቁ የአንገር ደን፣ የጊዳ ፍል ውሃ እና ለምለም የቡና ተራሮች ለጎብኚዎች ልዩ ድባብ የሚፈጥሩ ሀብቶች ናቸው።
ይህንን የቱሪዝም ጸጋ የሚያጅብ የዳበረ ባህላዊ እሴትም በከተማዋ በስፋት ይንጸባረቃል። የወለጋ መገለጫ የሆኑት ባህላዊ ምግቦች አንጮቴ፣ ጨጨብሳ እና ጩምቦ እንዲሁም በቅቤ የሚዘጋጀው ባህላዊው ቡነ ቀላ የነቀምቴን ማኅበረሰብ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል ያጎላሉ።
ወደ ነቀምቴ ጎራ ያለ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ቱሪስት እነዚህን ባህላዊ ምግቦች ከጥዑም ዜማ ጋር ሲያጣጥም ልዩ ትዝታ ይፈጥርለታል።
በአሁኑ ወቅት የነቀምቴን እና የአካባቢውን ገጸ በረከት ወደ ዕድል ለመቀየር የኦሮሚያ ክልል መንግሥትና የዞኑ ባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች ቅርሶችን ከመጠበቅ ባለፈ መዳረሻዎቹን በማልማት ከሌሎች የምዕራብ ኢትዮጵያ የቱሪዝም መስመሮች ጋር ለማስተሳሰር ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎችን ጀምረዋል።
የኩምሳ ሞሮዳ ቤተ-መንግሥት እና የወለጋ ሙዚየም እድሳት ተደርጎላቸው ለጎብኚዎች ክፍት መሆናቸው እንደ አንድ መልካም ጅምር ይታያል። በቀጣይም መሠረተ ልማቶች ተሟልተው የአካባቢው ባህላዊ ሙዚቃና ጭፈራዎች እንዲሁም የቡና ቱሪዝም በሚገባ ከለሙ፣ ነቀምቴና አካባቢው የሀገራችን ቀዳሚ የቱሪዝምና የኢኮኖሚ ማዕከል እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
ኅዳር 29 ቀን በጅማ ከተማ በሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል የወለጋን ቱባ ባህልና ቅርስ በማቅረብ፣ ከተለያዩ አካባቢዎች ለሚታደሙ እንግዶች የአካባቢውን ጸጋዎች የማስተዋወቅ ዕድል ይፈጠራል።
በመሐመድ ፊጣሞ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: