በመዲናችን አዲስ አበባ እየተከናወኑ ያሉት መጠነ ሰፊ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የከተማዋን ነባር ገጽታ በመቀየር፣ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር እና የንግድ እንቅስቃሴውን በማነቃቃት ረገድ ትልቅ ለውጥ እያመጡ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት 57 ሄክታር የሚሸፍነውን አዲሱን የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ባስመረቁበት ወቅት፣ በመዲናዋ የተጀመሩት የኮሪደር ልማት ሥራዎች ለከተማዋ ነዋሪዎች አዳዲስ ዕድሎችን ይዘው መምጣታቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ይህ የልማት እንቅስቃሴ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ እና ዘመናዊ የዲፕሎማሲ ማዕከል ከማድረግ ባለፈ፣ የነዋሪዎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያለመ ነው።
ከኮሪደር ልማቱ ዋና ዋና ትሩፋቶች አንዱ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠሩ ነው። በግንባታው ሂደት የተሰማሩ መሐንዲሶች፣ የቀን ሠራተኞች እና የግንባታ ግብዓት አቅራቢዎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
ከልማቱ መጠናቀቅ በኋላ በአካባቢዎቹ የተፈጠሩ አዳዲስ የንግድ ሥፍራዎች ደግሞ ለወጣቶችና ለነዋሪዎች ዘላቂ የገቢ ምንጭ እየሆኑ ይገኛሉ።
በተጨማሪም ሰፋፊ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገዶች፣ የመዝናኛ ፓርኮች እና ዘመናዊ የመብራት ዝርጋታዎች መሟላታቸው የከተማዋን የምሽት እንቅስቃሴ አድምቆ የንግድ ዝውውሩን ይበልጥ እንዲነቃቃ አድርጎታል።
ለዓመታት በተጨናነቁ መንገዶች እና በተበላሹ መሠረተ ልማቶች ስትፈተን የነበረችው አዲስ አበባ፣ በኮሪደር ልማቱ አማካኝነት ደረጃውን የጠበቀ የትራፊክ ፍሰት እና ጽዱ አካባቢ እየተላበሰች ነው።
የመንገድ ስፋት መጨመሩ እና የሕዝብ ማመላለሻ ተርሚናሎች መገንባታቸው የትራንስፖርት ችግርን ከማቃለል ባሻገር፣ የከተማዋን ውበትና የአየር ንብረት ተስማሚነት በማሻሻል ላይ ይገኛል። ልማቱ አዲስ አበባን ከዓለም አቀፍ ከተሞች ተርታ የሚያሰልፍ ታሪካዊ እርምጃም ጭምር ነው።
በመሆኑም በመዲናዋ ተጠናክሮ የቀጠለው የኮሪደር ልማት ሥራ የከተማዋን ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማሳደግ እና ዘመናዊ የከተማ አኗኗርን ለመገንባት የተያዘውን ራዕይ የሚያሳይ ሲሆን፣ ልማቱ የሁሉንም ነዋሪዎች ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶታል።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: