ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዜጎች በሀገራቸው ውስጥ የሚገኙ ውብ ስፍራዎችን የመጎብኘት ባህልን እንዲያዳብሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በተለይም አዲስ አበባ ክረምት እና ብርድ በሚሆንበት ወቅት እንደ ባሕር ዳር፣ አርባምንጭ እና ጅማ ያሉ ሞቅ ያሉ አካባቢዎች እንግዶችን ለመቀበል ሰፊ ዕድል እንዳላቸው ገልጸው፣ በአነስተኛ ወጪ በውጭ ሀገር የሚገኘውን እርካታ ሀገር ውስጥ ማግኘት እንደሚቻል አመልክተዋል።
በአዲስ አበባ የነበረውን የዘመናዊ የገበያ እና የመዝናኛ ማዕከላት (ሞሎች) ውስንነት ለመቅረፍ በርካታ ግንባታዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተለይም በለገሀር እና በአራዳ እየተገነቡ ያሉት ሞሎች በዚህ ዓመት እንደሚጠናቀቁ አብሥረዋል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት እና መዝናኛ ከመሆናቸውም ባለፈ ለሀገሪቱ ከፍተኛ የገበያ ዕድል እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል።
አክለውም "ጀምሮ መጨረስ መታደል ነው፤ ብዙዎች ያልማሉ፣ ጀምሮ መጨረስ ግን ለብዙዎች አልተሰጠም" ብልዋል፡፡
በሥራ ሂደት ላይ የሚያላግጡ አካላት ቢኖሩም የተሠራው ሥራ ግን ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቶቹ ለፍሬ እንዲበቁ ላገዘው ፈጣሪ እና ለተባበሩ ዜጎች ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ሀገርን የሚገነባው የራሱ ዜጋ በመሆኑ ሁሉም በትብብር እና በብርታት ልማቱን እንዲያስቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: