Search

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ምህዳር ለባለብዙ ዘርፍ ተጠቃሚነት

ዓርብ ኅዳር 11, 2019 122

አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት በዘመናችን የሀገራት የኢንቨስትመንት፣ ኢንዱስትሪ ዕድገት፣ አየር ንብረት ለውጥ መቋቋም ወሳኝ ሚና ይጨዋታል።

ብዙ አዳጊ ሀገራት ለነዳጅ ግዥ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማውጣት፣ በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ መዋዠቅ እና በአቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎል ተጋላጭ ሲሆኑ ይስተዋላል።

ኢትዮጵያ ይህን ተጋላጭነት ለመሻገር የተፈጥሮ ሀብቷን በስፋት እና በዕቅድ በማቀናጀት የምትገነባው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ምህዳር፤ ለኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት፣ ለትውልድ ቅብብሎሽ እና ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ሚዛን ጠንካራ መሠረት የሚጥል ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።

የውኃ፣ የንፋስ፣ የፀሐይ እና የጂኦተርማል የኃይል አማራጮችን አልምቶ መጠቀም ለነዳጅ የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለመቀነስ እና የክፍያ ሚዛንን ለማጠናከር ከፍተኛ ድርሻ አለው።

የሀገር ውስጥ የታዳሽ ኃይል ማመንጫዎች መስፋፋት የኢንዱስትሪ፣ የግብርና እና የትራንስፖርት ዘርፎችን ከውጭ ገበያ ድንገተኛ የዋጋ መለዋወጥ ይታደጋል።

በተለይም አነስተኛ ወጪ የሚጠይቅ እና አስተማማኝ ኃይል በአምራች ዘርፉ እና በኤሌክትሪክ ትራንስፖርት ላይ ሲውል የምርት ወጪን ይቀንሳል፤ የኢትዮጵያን ምርቶች ተወዳዳሪነትም ያሳድጋል።

የዛሬው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ኢንቨስትመንት የነገውን ትውልድ ሕይወት የሚቀርፅ ስትራቴጂያዊ ቅርስ ነው።

የተራቆቱ መሬቶችን ማገገም፣ የደን ሽፋንን ማሳደግ እና የከተማ አረንጓዴ ቦታዎችን ማስፋፋት ለሚቀጥሉት ትውልዶች መኖሪያነት ምቹ፣ ለም እና የተረጋጋ ምህዳር ያስረክባል።

የአፈር መሸርሸርን መከላከል እና የዝናብ ሥርጭትን ማረጋጋት የገጠሩን ማኅበረሰብ ገቢ እና የምግብ ዋስትና በዘላቂነት ያቆያል።

በተጨማሪም በታዳሽ ኃይል ዝርጋታ፣ በአግሮ-ፎረስትሪ፣ በአረንጓዴ የከተማ ልማት እና በኢኮ-ቱሪዝም ዘርፎች ለወጣቶች ሰፊ የሥራ እድሎች ይፈጠራሉ።

የአየር ንብረት ለውጥ ድንበር የማይገድበው ዓለም አቀፋዊ ፈተና ነው። የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በዓለም አቀፍ ደረጃ የካርቦን ልቀትን በመቀነስ፣ ብዝኃ ሕይወትን በመጠበቅ እና በቀጣናዊ የኃይል ትስስር በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

ይህም ኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት አርአያ ከማድረግ ባለፈ ዘላቂ የብልጽግና ጉዞዋን በጽኑ መሠረት ላይ ያቆማል።

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: