ለኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ ከዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ ከብሔራዊ ጥቅም፣ ከሉዓላዊነት እና ከትውልድ ተሻጋሪ ብልጽግና ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ስትራቴጂያዊ አጀንዳ ነው።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከሕዝብ ብዛት ቀዳሚ ከሆኑ ሀገራት አንዷ ብትሆንም የባሕር በር አልባ መሆኗ በወጪ ንግድ፣ በትራንስፖርትና በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ትሥሥሯ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል።
እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በድል ማጠናቀቅ የቻለችው ኢትዮጵያ፣ በብሔራዊ አንድነት እና ቁርጠኝነት የባሕር በር ተጠቃሚነቷን ማረጋገጥ እንደምትችል በተግባር እያሳየች ነው።
ኢትዮጵያ በጂኦግራፊያዊ አቀማመጧና በረጅም ታሪኳ የባሕር በር ባለቤት ሆና ኖራለች። ሆኖም በውስጥና በውጭ ኃይሎች ተጽዕኖ ምክንያት ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የባሕር በር አልባ ሆና ቆይታለች።
ይህ ሁኔታ የሀገራችንን የንግድ ተወዳዳሪነት በመገደብ ለውጭ ጭነቶች ከፍተኛ ወጪ እንዲወጣ አድርጓል። በተጨማሪም የደኅንነትና የሕልውና ጥቅሞችን በመፈታተን የኢኮኖሚ ነጻነቷን ሲፈትን ቆይቷል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የትሥሥርና የጋራ ተጠቃሚነት መርሆዎች እየጎሉ በመጡበት ወቅት፣ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ማንሳታቸው የኢትዮጵያን አቋም ፍትሐዊነት ይበልጥ ያጠናክረዋል።
የባሕር በር ተጠቃሚነት መረጋገጥ የገቢና የወጪ ምርቶችን የማጓጓዣ ወጪና ጊዜ በመቀነስ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች በተሻለ ዋጋ እንዲቀርቡ ያግዛል። በዚህም አዳዲስ የኢንቨስትመንትና የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር የሀገራችንን ኢኮኖሚያዊ አቅም ከፍ ያደርጋል።
ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በተጨማሪ ለቀጣናዊ ሰላም፣ መረጋጋትና የንግድ ትሥሥር ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል። በመሆኑም የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ጥያቄ የዘመናት የፍትሕ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ለመጪዎቹ ትውልዶች የልማትና የብልጽግና መሠረት የሚጥል ነው።
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሀገሩን የባሕር በር ባለቤትነት በባለቤትነት ስሜት በመያዝ፣ በጋራና በቁርጠኝነት እውን እንዲሆን ታሪካዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: