በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጉዞ ውስጥ ወሳኝ ምዕራፍ የሚከፍቱ አምስት ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች በከፍተኛ ፍጥነት እየተገነቡ ይገኛሉ።
ከ22 ቢሊዮን ዶላር በላይ በጀት የተያዘላቸው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የጎዴ ማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ግድብ፣ የአዋሽ-ወልዲያ-ሐራ ገበያ ባቡር መስመር እና የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ በአቪዬሽን፣ በኬሚካል፣ በንጹሕ ኃይል እና በትራንስፖርት ዘርፎች ዘላቂ የኢኮኖሚ መሠረት ለመጣል ያለሙ ናቸው።
የመደመር መንግሥት የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አካል የሆኑት እነዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ የሚያመጡት ለውጥ የሚጨበጥ ይሆናል።
በዋናነትም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለማቃለል እና ኢትዮጵያን ቀጣናዊ የኤክስፖርት ማዕከል ለማድረግ የሚኖራቸው ድርሻ እጅግ የላቀ ነው።
ለግንባታቸው ስኬትም በአክሲዮን ኢንቨስትመንት፣ በኤክስፖርት ክሬዲት ዋስትና እና በባለብዙ ወገን የፋይናንስ ቅንጅት እንዲመሩ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል።
በአፈጻጸም ረገድ የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ግድብ አጠቃላይ ግንባታ ከ78 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን፣ የመጀመሪያ ተርባይን ሙከራ በ2020 ዓ.ም መጨረሻ፣ ሥራውን ሙሉ በሙሉ የማጠናቀቅ ደግሞ በ2021 ዓ.ም ዕቅድ ተይዞ ግንባታው እየተፋጠነ ይገኛል።
1 ሺህ 800 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጨው ይህ ግድብ፣ የከፍተኛ ቮልቴጅ ማስተላለፊያ መስመሮችን በ2022 ዓ.ም ወደ 30 ሺህ ኪሎ ሜትር ለማሳደግ እና የኃይል ሥርጭት ብክነትን ለመቀነስ ከተያዘው ዕቅድ ጋር ተዳምሮ የኢንዱስትሪውን እና የኃይል ኤክስፖርት አቅርቦትን በእጅጉ ያጠናክራል።
በግብርናው ዘርፍ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት የጎዴ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ጥቅምት 2018 ዓ.ም ተጀምሮ 24 ሰዓት እየተፋጠነ ይገኛል።
ከዚህም ባለፈ ከጎልደን ኮንኮርድ ግሩፕ ጋር የ4.2 ቢሊዮን ዶላር የ25 ዓመት የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት ስምምነት ተፈጽሞ በ2021 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው። ፋብሪካው በዓመት 3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ዩሪያ እና 2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ማምረት ሲጀምር፣ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለማዳበሪያ ግዥ የምታወጣውን ከ1.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት ከ2.25 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ትርፍ ምርት ለምሥራቅ አፍሪካ ገበያ ታቀርባለች።
በተመሳሳይ በጥቅምት 2018 ዓ.ም መሠረተ ድንጋይ የተጣለለት የ2.5 ቢሊዮን ዶላር የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ በዓመት 3.5 ሚሊዮን ቶን የማጣራት አቅም ይኖረዋል።
ምዕራፍ አንድን በ2020 ዓ.ም መጨረሻ ለማጠናቀቅ የታቀደለት ይህ ፕሮጀክት፣ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለተጣራ ነዳጅ የምታወጣውን ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወጪ በመቀነስ 70 በመቶ የሚሆነውን የሀገር ውስጥ ፍላጎት ይሸፍናል።
በአቪዬሽን ዘርፍ ደግሞ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመሬት ዝግጅቱን 24 ሰዓት እየሠራ ሲሆን፣ ለቀጣይ የግንባታ ምዕራፍ ደግሞ በአራት ዋና ዋና የግንባታ ፓኬጆች የቅድመ-ብቃት ማጣሪያውን አጠናቅቆ የሥራ ተቋራጭ ምርጫ ሂደት ላይ ይገኛል።
በ2022 ዓ.ም የመጀመሪያው ምዕራፍ ሲጠናቀቅ በዓመት 60 ሚሊዮን መንገደኞችን፣ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ደግሞ ባለ አራት ማኮብኮቢያ ሆኖ እስከ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል።
ይህም የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ጫና በማቃለል የኢትዮጵያን የአፍሪካ የአቪዬሽን ማዕከልነት፣ የቱሪዝም እና የሎጂስቲክስ እንቅስቃሴ ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል።
በትራንስፖርት ዘርፍ 392 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የአዋሽ-ወልዲያ-ሐራ ገበያ የኤሌክትሪክ ባቡር መስመር በሰሜኑ ግጭት የደረሰበትን ጉዳት የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በራሱ ባለሙያዎችና ማሽነሪዎች እያደሰው ይገኛል።
ከ270 ኪሎ ሜትሩ የአዋሽ-ኮምቦልቻ ክፍል ውስጥ 70 ኪሎ ሜትር ያህሉ ተጠግኖ ለሙከራ ጉዞ ዝግጁ ተደርጓል፡፡ ሙሉ መስመሩን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዷል።
በዓመት 10 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የመጫን አቅም ያለው ይህ መስመር የመካከለኛውን እና የሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያን የንግድ እና የግብርና ኮሪደር ከአዋሽ-ጅቡቲ መስመር ጋር በማገናኘት የትራንስፖርት ጊዜን እና ወጪን በእጅጉ ይቀንሳል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች በግንባታ ሂደት ላይ እያሉም ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር እና የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን በማነቃቃት ላይ ናቸው።
በማክሮ ኢኮኖሚ ደረጃም የማዳበሪያ እና የነዳጅ ምትክ ምርቶች በሀገር ውስጥ መመረታቸው የንግድ ሚዛን ጉድለትን በማጥበብ፣ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር እና የንግድ ባንኮችን የውጭ ምንዛሪ ክምችት ጫና ለማቃለል ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።
የዕዳ መልሶ ማዋቀር ሂደት እየተጠናቀቀ ባለበት በዚህ ወቅት፣ እነዚህን ሜጋ ፕሮጀክቶች ማጠናቀቅ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከውጭ ጥገኝነት ራስን ወደመቻልና ወደ ቀጣናዊ ተወዳዳሪነት የሚያሸጋግር ታሪካዊ እርምጃ ነው።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: