Search

አፍሪካ ታሪኮቿን ወደ ተግባር የምትቀይርበት ጊዜ አሁን ነው፡- የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ

ዓርብ ኅዳር 18, 2019 44

አፍሪካ ብዙ የምትተርካቸው ታሪኮች እንዳሏትና ወደ ተግባር የምትቀይርበት ጊዜ አሁን መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ ገለጹ።

የአፍሪካ ኦዲዮቪዥዋል ኢንዱስትሪ ሥርዓትን ከእቅድ ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችል መድረክ እና አፍሪካ ያላትን የፊልም ተሰጥኦና ታሪክ ወደ ዘላቂ ኢንዱስትሪ ለመለወጥ የሚያስችል ውይይት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

“የአፍሪካን ኦዲዮቪዥዋል ኢንዱስትሪ ስርዓትን መገንባት ከእቅድ ወደ ተግባር” በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀው መርሐ ግብሩ የ2026 ሁለተኛ ዙር መድረክ ሲሆን፣ ከአፍሪካና ከመላው ዓለም የተውጣጡ የዲፕሎማቲክ ተወካዮች፣ የፈጠራ ዘርፍ ባለሙያዎች፣ ደራሲዎች፣ የፊልም ባለሙያዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የትምህርት አጋሮች፣ የፊልም ባለሙያዎች፣ ፕሮዲውሰሮችና ዳይሬክተሮች ተሳትፈዋል።

መርሐ ግብሩ በኢትዮጵያ ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ በብሪታንያ ኤምባሲ፣ በኡጋንዳ ሪፐብሊክ ኤምባሲ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የመዝናኛ ተቋም አርክውድ ኢንተርቴይመንት አስተባባሪነት ኅዳር 19 በሚካሄድ የአልባሳት ትርዒት ይጠናቀቃል።

የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ ለኪነጥበብ ዘርፍ ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ “አፍሪካ ብዙ የምትተርካቸው ታሪኮች አሏት፤ እነዚህን ታሪኮች ወደ ተግባር የምትቀይርበት ጊዜ አሁን ነው” ብለዋል።

በመድረኩ ተሰጥኦና ታሪክ መኖሩ ብቻ የፊልም ኢንዱስትሪውን ሊያሳድግ እንደማይችል ተገልጿል።

አፍሪካ ያላትን አቅም ወደ ተግባር መቀየር የዘመናችን ኃላፊነት እንደሆነ እና ሴቶችና ወጣቶች በፊልም ዘርፍና በአመራር ያላቸውን ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚገባ ተመላክቷል።

የፊልም ኢንዱስትሪው ለመዝናኛ ብቻ የሚውል ሳይሆን፣ ባህልን የሚያስተዋውቅና ሀገርን የሚገነባ መሆኑም ተጠቁሟል።

በዳግማዊ ሲሣይ

 

 

 

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: