Search

የኢትዮጵያ የቀጣናዊ ዲፕሎማሲ ዕይታ እና የአፍሪካ ቀንድ እውነታ

ዓርብ ኅዳር 18, 2019 51

“ጉርብትናን መወሰን ብንችል ጥሩ ነበር፤ አይቻልም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያደረጉት ንግግር፣ የአፍሪካ ቀንድን ውስብስብ ጂኦ-ፖለቲካዊ እውነታ በአንድ አረፍተ ነገር የገለጸ ነው።

በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ውስጥ ሀገራት ወዳጆቻቸውን መምረጥ ይችላሉ፤ መልክዓ ምድር የጻፈውን ድንበርና ታሪክ ያቆራኘውን ጉርብትና ግን በምኞት መቀየር አይቻልም።

አንዴ ከተፈጠሩ በኋላ ከፋም ለማም ተባብሮ መኖር የግድ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ የጎረቤት ሀገራትን ጉዳይ የዲፕሎማሲ ምርጫ ሳይሆን እንደ ሕልውና እና የጋራ ደኅንነት ጥያቄ እንደምትመለከተው አስገንዝበዋል።

ይሁን እንጂ በአፍሪካ ቀንድ የሚታየው ወቅታዊ ጂኦ-ፖለቲካዊ ሁኔታ፣ ይህ ተፈጥሯዊ ትሥሥር በቀላሉ እንዳይራመድ የሚያደርጉ የውጭ እጆችና ጫናዎች የበዙበት ነው።

በቀጣናው የሚገኙ አንዳንድ የጎረቤት ሀገራት አመራሮች የራሳቸውን ሕዝብ ዘላቂ ጥቅምና መረጋጋት ከማስቀደም ይልቅ፣ የሦስተኛ ወገኖችን ፍላጎትና ጫና ተሸክመው መገኘታቸው ቀጣናዊ ችግሮችን አራዝሟል።

በተለይም የሱዳን እና የኤርትራ አመራሮች የግብፅን ታሪካዊና ጂኦ-ፖለቲካዊ ፍላጎት አስፈጻሚ ሆነው መቆማቸው በቀጣናው ላይ የውክልና ውጥረትን በመፍጠር የሰላምና የልማት ጉዞውን ፈተና ውስጥ ከቶታል። የሩቅ ኃይሎች ቀጣናውን የፉክክር አውድማ ሲያደርጉትም ዋነኛ ተጎጂው የአፍሪካ ቀንድ ሕዝብ ሆኗል።

ኢትዮጵያ የጎረቤቶቿን አመራሮች ወቅታዊ አቋምና የውጭ ጫና እየተመለከተች እጇን አጣጥፋ አልተቀመጠችም። የሱዳን፣ የሶማሊያ፣ የኤርትራም ሆነ የሌሎች ጎረቤቶቿ ሰላም የራሷ ሰላም መሆኑን በጽኑ በማመን፣ ለቀጣናው መረጋጋት እስከ ደም መስዋዕትነት ድረስ ዋጋ ስትከፍል ኖራለች፤ ዛሬም ቀጥላበታለች።

በሱዳን የተከሰተውን አውዳሚ ጦርነት በውይይት ለመፍታት ሁሉንም ተፋላሚ ኃይሎች በገለልተኝነት ለማቀራረብ ዲፕሎማሲያዊ አቅሟን ሳትሰስት እያዋለች ትገኛለች።

በሶማሊያ አሸባሪነትን ለመመከት እንዲሁም በደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነቶች እውን እንዲሆኑ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና ዲፕሎማሲ ግንባር ቀደም ሚና ተጫውታለች።

“ከምንጭ የተጠጋ ዋርካ ሁሌም ይፈካል” እንደሚባለው፣ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ካላትና በታዳሽ ኃይል፣ በመሠረተ ልማት እና በኢኮኖሚ እየገሰገሰች ካለችው ኢትዮጵያ ጋር በቅንነትና በወንድማማችነት የሚቆም ጎረቤት ሁሉ በጋራ ይለመልማል።

ኢትዮጵያ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና ከሌሎች ታዳሽ ምንጮች የምታመነጨውን ንጹሕ የኤሌክትሪክ ኃይል ለሱዳን፣ ለኬንያ እና ለጂቡቲ በማቅረብ ቀጣናውን በብርሃን ከማስተሳሰሯ ባለፈ፣ የመንገድ፣ የባቡር እና የቴሌኮም መስመሮችን ከጎረቤት ሀገራት ጋር በማገናኘት ላይ ትገኛለች።

በሃና ምንዳሁን

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: