በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቱሉ ዲምቱ ወረዳ የገቢዎች ቢሮ ሠራተኛ መስለው ሲያጭበረብሩ የነበሩ ሁለት ተጠርጣሪዎች በሕዝብ ጥቆማ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
ተጠርጣሪዎቹ የንግድ ቤቶችን እየተዘዋወሩ "ያለደረሰኝ ግብይት ፈጽማችኋል" በሚል የ100 ሺህ ብር ቅጣት እንደሚጣልባቸው ያስፈራራሉ። ከዚያም ለመንግሥት ከሚከፈለው ቅጣት ይልቅ 50 ሺህ ብር እንዲሰጧቸው በመጠየቅ ገንዘብ ሲቀበሉ ቆይተዋል።
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሕግ ተገዢነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ፓርቲ ንጉሤ እንደገለጹት፣ ግለሰቦቹ እውነተኛ ማንነታቸውን በመደበቅ የሐሰት መታወቂያ ተጠቅመዋል።
ምትኩ ጋዲሳ "አየለ ጥላሁን" በሚል፣ ጌታሁን ደቻሳ ደግሞ "አድማሱ ከበደ" በሚል ሐሰተኛ ስምና መታወቂያ ሲንቀሳቀሱ በነጋዴዎች ጥቆማ ተይዘዋል።
በእጃቸውም ከገቢዎች መታወቂያ በተጨማሪ የመሬት ባለሙያ መሆናቸውን የሚያሳይ ሌላ የሐሰት መታወቂያ ተገኝቷል።
ተጠርጣሪዎቹ በሕግ ቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ይገኛል። አቶ ፓርቲ ከዩኒፎርም ውጪ የሚንቀሳቀሱ የገቢዎች ሠራተኞች "ባርኮድ" ያለው መታወቂያ እንደሚይዙ ቢሮው በላከልን መግለጫ ጠቅሷል።
ነጋዴዎች መታወቂያ በመጠየቅ እና ባርኮዱን በስልክ በመቃኘት ማንነት እንዲያረጋግጡ መክረዋል።
ተመሳሳይ ጥርጣሬ ሲያጋጥምም ለፀጥታ አካላት ወይም በ7075 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: