በሬ ጭኖ ሲጓዝ የነበረ ተሽከርካሪ በወላይታ ዞን ዱጉና ፋንጎ ወረዳ ኮይሻ ቀበሌ ሲደርስ በመገልበጡ አሽከርካሪው እና ረዳቱ ሕይወታቸው ማለፉን ፖሊስ አስታውቋል።
የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ኤሊያስ ሜንታ አደጋው የደረሰው ትናንትና ሌሊት 7፡30 ገደማ መሆኑን ተናግረዋል።
የጭነት ተሽከርካሪው ከኮንሶ ወደ ሞጆ ሲጓዝ እንደነበር አንስተው፤ በርካታ በሬዎችን ጭኖ እንደነበርም አስረድተዋለ።
በተሽከርካሪው ላይ የነበሩ 15 የደለቡ በሬዎችም ሕይወታቸው ማለፉን ገልጸው፤ 2 በሬዎች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው መትረፋቸውንም ምክትል ኮማንደሩ ገልጸዋል።
መንገዱ ቁልቁለት እና ጠመዝማዛ ከመሆኑም በላይ ፍጥነት እና የጭነት ብዛት በአካባቢው በተደጋጋሚ ለሚከሰተው አደጋ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል።
አሽከርካሪዎች ምን ጊዜም ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በተመስገን ተስፋዬ