Search

የ1958ቱ የሙኒክ አውሮፕላን አደጋ እና የማንችስተር ዩናይትድ አሳዛኝ የታሪክ ቀን

ረቡዕ ነሐሴ 21, 2017 58

በማንቸስተር ዩናይትድ ታሪክ ውስጥ እጅግ አሳዛኝ እና ልብ የሚሰብር ቀን ሆኖ ተፅፏል የ1958ቱ የሙኒክ አውሮፕላን አደጋ። በቀድሞ ስሙ የአውሮፓ ዋንጫ በሚባለው ውድድር ተሳታፊ የነበረው ማንችስተር ዩናይትድ የወቅቱን ጠንካራ ስብስብ ይዞ እስከ ግማሽ ፍጻሜ ቢደረስም መጨረሻው ግን ሀዘን ሆኗል፡፡
 
የየሀገራቱ የሊግ አሸናፊዎች ብቻ ይሳተፉበት በነበረው የጨዋታ ቅርጽ እንግሊዝን በብቸኝነት የወከለው ማንችስተር ዩናይትድ ከቅድመ ማጣሪያው ጀምሮ በርካታ ግቦች እያስቆጠረ ለሩብ ፍጻሜው ይደርሳል፡፡
በሩብ ፍጻሜው ከሰርቢያው ሬድስታር ቤልግሬድ የተገናኘው ዩናይትድ ኦልድ ትራፎርድ ላይ ያደረገውን የመጀመር ጨዋታ 2 ለ 1 የመልሱን ጨዋታ ደግሞ ቤልግሬድ ላይ 3 አቻ አጠናቆ በድምር ውጤት 5 ለ 4 በማሸነፍ የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
 
የማንችስተር ዩናይትድን የወደፊት የእግር ኳስ ጉዞ ወደ ሌለ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግር ተስፋ የተጣለበት እና በክለቡ አሰልጣኝ ማት በዝቢ ስም ከተቋቋመው የእግር ኳስ ፕሮጀክት ለትልቁ የአውሮፓ መድረክ ውድድር በርካታ ወጣቶች ተመርጠዋል፡፡
 
በዝቢ ቤቢ በሚል ስም ከሚታወቀው የማንችስተር ዩናይትድ ወጣት ቡድን የተመረጡ ከዋክብትን የያዘው ስብስብ መነሻውን ሰርቢያ አድርጎ ወደ እንግሊዝ ጉዞ ይጀምራል፡፡ ንብረትነቱ የእንግሊዝ አየር መንገድ የሆነው አውሮፕላን 44 ተሳፋሪዎች ይዞ ከቦታው በሰላም ከተነሳ በኋላ ነዳጅ ለመሙላት ጀርመን ሙኒክ ያርፋል፡፡
 
ሰላማዊ የነበረው አውሮፓላኑ ከሙኒክ ተነስቶ በድጋሜ ወደ እንግሊዝ ለመብረር ቢሞክርም የአደጋው ቅድመ ማስጠንቀቂያ ይመስል ከሙኒክ-ሪም መሬትን ትቶ ይነሳ ዘንድ ከአንድም ሁለት ጊዜ ቢሞከርም ሊነሳ አልቻለም፡፡
 
አብራሪዎቹ በሁኔታው ግራ ቢጋቡም ተስፋ ሳይቆርጡ በ 3ኛው ሙከራ አውሮፕላኑ የሙኒክን መሬት ለቆ ወደ ሰማይ ከፍ ማለት ጀመረ፡፡ ነገር ግን ብዙም ሳይጓዝ ገና መሬትን እንደለቀቀ የማንችስተር ዩናይትድን የቡድን አባላት ጨምሮ 44 ሰዎችን የያዘው አውሮፕላን ተከሰከሰ፡፡በአደጋውም ህወታቸው ካለፈው 23 ሰዎች 8ቱ የዩናይትድ ተጫዋቾች እና ሦስቱ የቡድኑ አባላት ነበሩ፡፡
በአውሮፓ መድረክ ላሳዩት ድንቅ ብቃት የክለቡ ደጋፊዎች ሊያመሰግናቸው የሚጠብቃቸው እነዛ ከዋክብት በሙኒክ እንደወጡ ቀሩ። ይህ ቀን በማንችስተር ዩናይትድ ብቻ ሳይሆን በእግር ኳስ አፍቃሪያን ዘንድ የሚታወስ እና የሚዘከር ሆነ፡፡
 
በወቅቱ ከአደጋው የተረፉት እንደ ሰር ቦቢ ቻርልተን አይነት ዕድለኛ ተጫዋቾች በቀያይ ሳይጣናቱ ቤት ታሪክ ሰርተው አልፈዋል፡፡ ከዋይኒ ሩኒ በመቀጠል የማንችስተር ዩናይትድ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሰር ቦቢ ቻርልተን ከሁለት አመት በፊት ህይወቱ ማለፉ የሚታወስ ነው፡፡ በተቃራኒው ከአደጋው ቢተርፉም በደረሰባቸው ከባድ የአካል ጉዳት ምክንያት ዳግም ወደ እግር ኳስ ያልተመለሱም ብዙ ናቸው፡፡
 
አስከፊው የሙኒክ አደጋ ከተከሰተ 66 ዓመታት ቢያልፉም እነዚያ ከዋክብት አሁንም በበርካታ ደጋፊዎች ልብ ውስጥ የተቀመጡ ናቸው፡፡ታሪካቸውም በስብርባሪው አውሮፕላን ውስጥ ተደብቆ የቀረ አይደለም፡፡
 
በሴራን ታደሰ