በአዲስ የጨዋታ ቅርፅ መካሄድ ከጀመረ 2ኛ ዓመቱ ላይ የሚገኘው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የዚህ ዓመት ድልድል ነገ በሞናኮ ይፉ ይደረጋል።
36 ክለቦች በሚሳተፉበት የሊግ ፎርማት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በስድስት ክለቦች ይወከላል።
የዩሮፓ ሊግ አሸናፊው ቶተንሀም ሆትስፐርን ጨምሮ ሊቨርፑሉ አርሰናል ማንችስተር ሲቲ ቼልሲ እና ኒውካስትል ዩናይትድ ተሳታፊ ክለቦች ናቸው።
ለ71ኛ ጊዜ በሚደረገው የአውሮፓ ትልቁ ውድድር ስፔን ጣልያን እና ጀርመን እያንዳንዳቸው በአራት ክለቦች የሚወከሉ ሲሆን ፈረንሳይ በሦስት ክለቦች ይወከላል።
የድልድል ቋቱ ቀደም ብሎ የሚታወቅ ሲሆን በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የክለቦቹ ደረጃ መሰረት ትልልቆቹ ቡድኖች በቋት አንድ ላይ ይገኛሉ።
ሪያል ማድሪድ፣ ባርሴሎና፣ ማንችስተር ሲቲ፣ ሊቨርፑል፣ ቼልሲ፣ ቦርሲያ ዶርተሙንድ፣ ባየር ሙኒክ፣ ኢንተር ሚላን እና ፒኤስጂ በቋት አንድ ላይ የሚገኙ ናቸው።
በሊግ ጨዋታ ቅርጽ በሚካሄደው ውድድር ከ36 ክለቦች ከ1ኛ እስከ 8ኛ ሆነው የሚያጠናቅቁት በቀጥታ ጥሎ ማለፉን የሚቀላቀሉ ሲሆን ከ9ኛ እስከ 24ኛ ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁ ደግሞ በእርስ በእርስ ጥሎ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ 16ቱን የሚቀላቀሉ ይሆናል፡፡
አንድ ክለብ 8 ጨዋታዎችን በሚያደርግበት የጨዋታ ቅርጽ አራቱን በሜዳው እና አራቱን ደግሞ ከሜዳው ያደርጋል፡፡
በአንተነህ ሲሳይ