በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥናት መሰረት፤ የባሕር በር ባላቸው እና በሌላቸው ሐገራት መካከል ከ10 - 20 ፐርሰንት የሚሆን የኢኮኖሚ የእድገት ልዩነት አለ።
ከኢቲቪ ዳጉ ፕሮግራም ጋር ቆይታ ያደረጉት የታሪክ መምህር እና ተመራማሪው ኢብራሂም ሙሉሸዋ (ዶ/ር)፥ የባሕር በር ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ቁልፍ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ለዘመናት የነበራት ሀገር እንደሆነች እና ስትታገልበት የኖረችው ጉዳይ መሆኑን አንስተው፤ ባሕር ለአንድ ሀገር መሸጋገሪያ ብቻ አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ያሉት።
የባሕር በር ያላቸው ሐገሮች የባሕር በራችውን ከማጓጓዣነት በዘለለ ለደህንነት እና በርካታ ዘርፎች እንደሚጠቀሙበትም ገልጸው፤ በተለይም የነቃ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው የባሕር በር የእራሱን አስተዋፅኦ እንድሚያበረክት ጠቁመዋል።
ቱሪዝም ለአንድ ሀገር የኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ መሆኑን አንስተው በዓለም ላይ በርካታ የቱሪዝም ፍሰት ያለባቸው ሀገራት የባሕር በር ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
መሬት ላይ የማይገኙ ባሕር በመኖሩ ብቻ የሚገኙ በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች መኖራቸውንም ነው ያነሱት።
አክለውም “የባሕር በር የብሔራዊ ደሕንነት ዋና አስኳል ነው” ብለዋል።
የባሕር በር ከአንድ አሕጉር ወደ ሌላ አሕጉር የምንሸጋገርበት ድልድይ በመሆኑ ከዓለም ጋር የሚኖረን የንግድ ግንኙነት እና የኢኮኖሚ ትስስር ከፍተኛ ለውጥ እንዲኖረው ማድረግ ያስችላል ነው ያሉት።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ