በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ ዞን ሎማ ቦሳ ወረዳ ሻይቲ ፉላሳ ቀበሌ ነው የተወለደችው ምርታለም ዳሮታ።
በ2005 ዓ.ም ነበር በቤት ሠራተኝነት ወደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ያቀናችው።
ከተጠቀሰው ዓመተ- ምህረት ጀምሮ በሆሳዕና ከተማ 18 ማዞሪያ በርበራ በሚባል አካባቢ በግለሰብ ቤት ውስጥ ለ12 ተከታታይ ዓመታት መቆየቷን የዳውሮ ዞን ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር ብርሃኑ ባይከዳኝ ይገልጻሉ።
ዳሩ ግን በቆይታዋ ለከፍተኛ እንግልት መዳረጓን ነው ፖሊስ ያስታወቀው።
በተጎጂዋ ላይ የአካል መጉደል፣ ድብደባ እና የስነ-ልቦና ጫናዎችን እንደደረሰባት በምርመራ መጣራቱንም ምክትል ኢንስፔክተር ብርሀኑ አብራርተዋል።
ለ12 ተከታታይ ዓመታት ወደ ቤተሰቧቿ ሳትመጣ የቆየችው ምርታለም በተጠሪጣሪዎቹ ስለደረሰባት ጥቃት የዳውሮ ዞን ፖሊሲ ከሀዲያ ዞን ፖሊስ መምሪያ እና ከሆሳዕና ከተማ ፖሊስ መዋቅሮች በጋራ ምርመራ እያደረጉ መሆኑን ምክትል ኢንስፔክተሩ ገልፀዋል።
ጥቃት አድርሰዋል ተብለው የተጠረጠሩ አሰሪዋ እና ባለቤቷ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አመላክተዋል።
ወይዘሪት ምርታለም በአሁኑ ሰዓት በሆሳዕና ንግስት እሌኒ መሐመድ መታሰቢያ ጠቅላላ ሆስፒታል የሕክምና እርዳታ እያገኘች እንደሆነም ፖሊስ ገልጿል።
በወንጀል ድርጊቱ ላይ ሰፊ ምርመራዎችን በማከናወን የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ይሰራል ሲሉም ምክትል ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል።
በወንጀል ድርጊቱ የማጣራት ሂደት የሃዲያ ዞን ፖሊስ መምሪያ፣ የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽ/ቤት እንዲሁም የሃዲያ ዞን ፍትህ መምሪያ እና የሴቶችና ሕፃናት መምሪያ ቀና ትብብር ማድረጋቸውንም ገልጸዋል ምክትል ኢንስፔክተሩ።
ጉዳቱን ማንም ይፈጽመው ማንም ሰብዊነትን የተጋፋ መሆኑን ጠቁመው፤ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተጀመረው የተቀናጀ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ምክትል ኢንስፔክተሩ ዜጎች ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን በመከላከል ከፍተኛ ሥራ ሊሰሩ እንደሚባም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በሰለሞን ባረና