Search

በተደረገልን ድጋፍ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ጀምረናል - የጎፋ ዞን ነዋሪዎች

ረቡዕ ነሐሴ 21, 2017 142

በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ አምና ሐምሌ ወር ላይ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ 249 ዜጎች መሞታቸው ይታወሳል።

በወቅቱ በርካቶች አዝነዋል ድጋፋቸውንም ለግሰዋል።

መንግሥት የአካባቢው ነዋሪዎች ለሌላ አደጋ እንዳይጋለጡ በሚል ወደተሻለ አካባቢ እንዲዛወሩ ድጋፍ አድርጓል።

በጎፋ ዞን ኬንቾ ቡርዳ ቀበሌ ሰፈራ ጣቢያ ቤት የተገነባላቸው ተፈናቃዮችም  በተደረገልን ድጋፍ የአምናውን አስከፊ አደጋ በመርሳት አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ጀምረናል ሲሉ ተናግረዋል። ።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር በጎፋ ዞን ኬንቾ ቡርዳ ቀበሌ ያስገነባቸውን 627 የተፈናቃይ ቤቶችን በነገው ዕለት አስመርቆ ያስረክባል።

አስተያየታቸውን ለኢቢሲ የሰጡት ነዋሪዎቹ በመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ በውሃ መሠረተ ልማት አቅርቦት እና በግብርናው ዘርፍ ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በተደረገላቸው ድጋፍ መደበኛ ኑሮ መጀመራቸውን የጠቀሱት ነዋሪዎቹ፤ የመብራት እና መንገድ መሠረተ ልማት በቀጣይ እንደሚሟላ ተስፋ እናደርጋለን ሲሉ ተናግረዋል።

ቤቶቹን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቀይ መስቀል ማሕበር በሰብዓዊ ድጋፍ በተገኘ ሃብት ኃላፊነት ወስዶ ያስገነባው ሲሆን፤ በነገው እለት የደቡብ ኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የርክክብ ስነ-ስርዓት ይካሄዳል ተብሏል።

 

በተመስገን ተስፋዬ