“ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ” ጥያቄ እና ቁጭት የወለደው የፅሑፍ ሥራ ነው ሲሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ይገልጻሉ፡፡
‘እኛ ለዴሞክራሲ አዲስ ሆነን ሳይሆን ፣ እያለን የረሳነው ስለሆነ ነው’ የሚል ሃሳብ ያለው መፅሐፍ መሆኑንም አንስተዋል።
“ሁሉ እያለን እደሌለን ለምን ሆንን? ፣ ከሺህ ዓመታት በፊት የነበረንን ኃያልነት ለምን አጣን? ፣ ታሪካችን ላይ የግጭት እና ያልተስማማንባቸው ጉዳዮች ስለምን ጎልተው ወጡ?” ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት የተፃፈ መሆኑን ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ያስረዳሉ።
ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) መፅሐፉን በተመለከተ በተለያዩ የሥራ መስኮች ከሚገኙ ባለሙያዎች እና ባለስልጣናት ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው ይህን ያሉት፡፡
ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ማለት የሁሉም መልክ መሆኑን የሚናገሩት ፀሐፊው።
ከግሪክ፣ ከቻይና፣ ከሮማ፣ ከሕንድ እና ከፐርሺያ ጋር አቻ የሆነ ስልጣኔ የነበራት ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ነጥረው መውጣት የሚችል የዴሞክራሲ እሴቶቿን መያዟን ይናገራሉ፡፡
ሀገራቱ በልካቸው የሰፉት የዴሞክራሲ ስርዓትም በጊዜ ሂደት የተበጀ እንጂ በመጀመሪያ ውጤታማ እንዳልነበር አስረድተዋል፡፡
መፅሐፉ እየተገበርን ያለውን ስርዓት እንሻር ሳይሆን ያለን የዴሞክራሲ ስርዓት፣ በታሪክ፣ በሥነ-ልቦና፣ በእሴት እና በሞራል መዋቅር እና ላይ የተመሰረት ለማድረግ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህም የሕዝብን ጥያቄ የሚመልስ ሆኖም ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮን የተላበሰ ስርዓት እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በአፎሚያ ክበበው