Search

የመንግስትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ፈቱ

ሓሙስ ነሐሴ 22, 2017 102


በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሲንቀሳቀሱ የነበሩ  ታጣቂዎች የሰላም ጥሪውን በመቀበል ትጥቃቸውን አስረከቡ።

የቀድሞ ታጣቂዎቹ የተሃድሶ ስልጠናን ለመውሰድ በብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የደብረብርሃን ያዊ ዲሞብላይዜሽን ማዕከልን ተቀላቅለዋል።

በትጥቅ ርክክቡና የተሃድሶ ሶልጠና የመክፈቻ ሥነ-ርዓቱ ላይ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፣  የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪና የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አሕመዲን መሐመድ (/) የአማራ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ እሸቴ የሱፍ (/)  እና የመከላከያ ሠራዊት ተወካዮች ተገኝተዋል።

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን እስካሁን ድረስ በተለያዩ ክልሎች 72 ሺህ 500 የቀድሞ ታጣቂዎችን የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት ወደ ህብረተሰቡ መመለስ እንደተቻለ ገልፀዋል። 

በሁለተኛው ዙርም በአማራ ክልል በሶስት የተሃድሶ ማሰልጠኛ ማዕከላት፤ ማለትም በጎንደር በኮምቦልቻና በደብረ ብርሃን 6ሺህ ታጣቂዎች ወደ ስልጠና ማዕከል መቀላቀላቸውን ኮሚሽነሩ ገልፀዋል። 

ትጥቃቸውን ፈተው ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለሚመለሱ ታጣቂዎች የሥራ መጀመሪያ የገንዘብ ድጋፍና የሥራ ዕድል መመቻቸቱንም አንስተዋል። 

በሌሎች አካባቢዎችም የፖለቲካ ጥያቄያቸውን በኃይል ለማስመለስ ነፍጥ ያነገቡ ወገኖች የሰላም ጥሪውን በመቀበል ወደ ህብረተሰቡ እንዲመለሱ ጠይቀዋል። 

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው፤ መንግስት ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፣ የሽግግር ፍትህና መሰል ተቋማትን በማቋቋም በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል። 

የትጥቅ ትግልን አማራጭ ያደረጉ ወገኖችም ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል። 

የተሃድሶ ስልጠናውን የተቀላቀሉ በትጥቅ ትግል የነበሩ አካላትም እስካሁን በነበሩበት የትጥቅ ትግል፤ ሕዝቡን አራሳቸውንና ሀገርን እንደጎዱ በመረዳት የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ትጥቃቸውን ማስረከባቸውን ገልፀዋል።

በቀጣይም የፖለቲካ ጥያቂያቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እና በሀገር ልማት ላይ ንቁ ተሳታፊ ለመሆን ቁርጠኛ ነን ነው ያሉት

በአስማረ ብርሀኑ