በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ማዕከል በሚሰጠው ነፃ የልብ ሕክምና የልጅነት ልባቸው ታክሞ ዛሬ ላይ በተለያዩ ጤና ተቋማት ልብ የሚያክሙ የጤና ባለሞያዎች ማፍራት መቻሉን የማዕከሉ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር ዳዊት እሸቱ ገለፁ።
በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ማዕከል ባለፈው ዓመት ብቻ ከ 40 በላይ የሚሆኑ ሕፃናት ወደ እስራኤል ሄደው እንዲታከሙ ማድረጉንም ነው ዶ/ር ዳዊት የገለፁት።
የአገልግሎት ስፍራዎች ለሕዝብ ግንኙነት ክፍት እንደሆኑት ሁሉ ማዕከሉ ከሰው ለሰው እንዲሁም ከታካሚ እና ሀኪም ግንኙነት ባሻገር ልብን ከልብ የሚገናኝበት ስፍራ መሆኑም ተገልጿል።
ዶ/ር ዳዊት እሸቱ በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ማዕከል የመጀመሪያው እና ብቸኛው ነፃ የልብ ሕክምና ማዕከል መሆኑን ገልፀው፣ ከግለሰብ አንስቶ እስከ ድርጅቶች ድረስ ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ እና ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
ማዕከሉ በሚሰጣቸው የነጻ የልብ ቀዶ ሕከምና አገልግሎቶች የሕጻናትን ጤና ከመመለሰ ባሻገር በሕጻናት ዕድገት እና ትምህርት ላይ አዎንታዊ አስተዋጽዖ በማበርከት ለቤተሰብም ከሥነ ልቦና ከማኅበራዊ እና ከኢኮኖሚያዊ ጫናዎች መታደግ ችሏል።
በሴራን ታደሰ