Search

በአማራ ክልል የተማሪዎች ምዝገባ በአንዳንድ አካባቢዎች 90 በመቶ ደርሷል፡- የክልሉ ትምህርት ቢሮ

ሓሙስ ነሐሴ 22, 2017 131

በ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በአማራ ክልል ተመዝግበው ትምህርት ይጀምራሉ ተብሎ የሚጠበቁት ከ7.4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ምዝገባው 91 በመቶ መድረሱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጌታቸው ቢያዝን ገልጸዋል፡፡ 

በመደበኛነት ምዝገባው ከነሃሴ 19 ጀምሮ ክልል አቀፍ በሆነ መልኩ እየተካሄደ ሲሆን አፈጻጸሙ በጣም ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ነው ኃላፊ ለኢቢሲ ዶትስትሪም የገለጹት፡፡

ለዚህ ውጤት መገኘትም በክልሉ ለትምህርት የደረሱ ልጆችን በሙሉ ወላጆች እንዲያስመዘግቡ በቅንጅት ለመስራት እንዲያስችል ከማን ምን ይጠበቃል በሚል ከባለድርሻ አካላት ጋር  ውይይትና ምክክር መካሄዱ ጠቃሚ ሆኗል ብለዋል።

በዚህም በአማራ ክልል መመዝገብ ያለባቸው ተማሪ በሙሉ እንዲመዘገቡ የክልል፣ የዞንና የወረዳ ትምህርት መምሪያ አመራሮች፣የመምህራን ማህበር አመራሮች፣ የተማሪ ወላጅ ተወካዮች ጋር መግባባት ላይ መደረሱንም ነው የነገሩን።

ወላጆች በአቅም እጥረት ምክንያት ልጆችን ከትምህርት ገበታቸው እንዳይርቁ ለማገዝ  የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶችና ድርጅቶች ጋር እየተሰራ መሆኑን ያነሱት አቶ ጌታቸው ቢያዝን ይህ ሂደት ተጠናክሮ መቀጠሉን ለኢቢሲ ዶትስትሪም ተናግረዋል፡፡

ዛሬ አራተኛ ቀኑን የያዘው የተማሪዎች ምዝገባ ነሃሴ 30 ቀን 2017 ዓ.ም የሚጠናቀቅ በመሆኑን የተቀመጠውን እቅድ ማሳካት ማሳካት እንደሚገባ ኃላፊው አሳስበዋል።

በመሀመድ ፊጣሞ