በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የመሬት መንሸራተት እና የናዳ አደጋ በዘላቂነት ለመከላከል ተራሮችን ማልማት እንደሚያስፈልግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር በክልሉ በመሬት መንሸራተት እና ናዳ ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ያስገነባቸውን 296 የመኖሪያ ቤቶች የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በተገኙበት አስረክቧል።
በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ጥላሁን፥ ክልሉ ለተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭ በመሆኑ፣ በሁሉም አካባቢዎች በአረንጓዴ ዐሻራ ልማት የተጀመረውን የተራራ ልማት አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ እና የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽን የቦርድ አባል አቶ አበራ ቶላ፥ ለተጎጂዎች የተደረገው ድጋፍ ለሌሎች አካባቢዎች ተምሳሌት እንደሚሆን ተናግረዋል።
አክለውም፥ በቀጣይ ጊዜያት ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሲከሰቱ በፍጥነት ድጋፍ ለማድረስ የክልሎችን ምላሽ የመስጠት አቅም እናሳድጋለን ብለዋል።
በተጨማሪም የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ተሳትፎና አቅም የማጎልበት ሥራ ይከናወናል ነው ያሉት።
ለተጎዱ ወገኖች ቤት ከመገንባት በተጨማሪ መደበኛ ኑሮ እንዲጀምሩ የገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም ዘር፣ ማዳበሪያ እና የአፕል ችግኝ መሰራጨቱን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ዱንዳ ናቸው።
የዕድሉ ተጠቃሚዎች በበኩላቸው በተደረገላቸው ድጋፍ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ በመጀመራቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው፤ በቀጣይ የመብራት እና የመንገድ መሠረተ ልማት እንዲሟላላቸው ጠይቀዋል።
በተመስገን ተስፋዬ
#EBCdotstream #South_Ethiopia #Landslide #ICRC #ERCS