ሰዎች ያደጉበትና የመጡበት መንገድ ለዛሬ ማንነታቸው መሰረት ይጥላል።
ደግነትና መልካምነትን እያየ ያደገ ሰው ደግሞ መልካም ነገሮችን ለመተግበር ሁሌም ዝግጁ ነው።
ዳዊት በቀለ ይባላል። የድሬድዋ ከተማ ኗሪ ሲሆን፤ በልጅነት አዕምሮው እናቱ ተርፏቸው ሳይሆን ካላቸው ላይ ለሰዎች ሲያከፍሉ እያየ በማደጉ ዛሬ ላይ ለብዙዎች ማረፊያ የሆነ ማዕከል ሊከፍት ችሏል።
የአሁኑ በጎ አድራጊ ዳዊት በልጅነቱ ኑሮን ለማሸነፍ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሰራ ያደገ ሲሆን፤ ዳቦ በሚሸጥበት ወቅት ለተቸገሩ ከመስጠት ጀምሮ ጎዳና ላይ የወደቁትን ያነሳ ነበር።
ከልጅነት እስከ ዕውቀት ለ20 ዓመታት ሰዎችን በመርዳት የኖረው ዳዊት፤ አሁን ላይ በድሬዳዋ ከተማ አረጋውያንን ለማገዝ ዳዊት የአረጋውያን መርጃ ማዕከልን ከፍቶ እየሠራ ይገኛል።
በማዕከሉ 235 አረጋውያን የሚገኙ ሲሆን፤ ከነዚህ በተጨማሪ ምግብ፣ አልባሳትና የንፅሕና መጠበቂያ በየቤታቸው የሚደርሳቸው በርካታ አረጋውያን መኖራቸውንም ዳዊት ይናገራል።
እኛ ኢትዮጵያውያን ከተጋገዝን ብዙ ችግሮችን ማቅለል እንችላለን የሚለው ዳዊት፤ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና የከተማዋ ነዋሪዎች ላደረጉለትና እያደረጉት ላለው ድጋፍ ሁሉ ምስጋናውን አቅርቧል።
በሰናይት ብርሀኔ
#EBCdotstream #Diredawa #Philanthropy #Charity