Search

ኢትዮጵያ ለቴምር ልማት ምቹ የሆነ እምቅ አቅም አላት - የቴምር ፌስቲቫል ተሳታፊዎች

ሓሙስ ነሐሴ 22, 2017 84

በአፋር ክልል እየተካሄደ ያለው ዓለም አቀፍ የቴምር ፌስቲቫል ተሳታፊዎች በአሳይታ ባካሄዱት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር የቴምር ችግኞችን ተክለዋል።

በዚሁ ወቅት በፌስቲቫሉ ለመሳተፍ በቴምር አምራችነታቸው ከሚታወቁ የተለያዩ ሀገራት ከመጡ ተወካዮች ጋር በቴምር ችግር አተካከል እና እንክብካቤ ዙሪያ የልምድ ልውውጥ ተካሂዷል።

የፌስቲቫሉ ተሳታፊዎች በአፋር ክልል በተደረገላቸው የእንግዳ አቀባባል እና መስተንግዶ በእጅጉ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ተሳታፊዎቹ ኢትዮጵያ ለቴምር ልማት ምቹ የሆነ እምቅ አቅም ያላት ሀገር መሆኗን በሰመራ ቆይታችን አፋርን ተዘዋውረን በማየት ማረጋገጥ ችለናል ብለዋል።

በአፋር ክልል ያለውን ሰፊ የመሬት እና የውሃ ሀብት በአግባቡ በመጠቀም የቴምር ምርትን ጨምሮ በምግብ ዋስትና ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን ሥራ ማከናወን እንደሚቻልም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

በቀጣይ በኢትዮጵያ የግብርና እና  የአግሮ-ኢንዱስትሪ ዘርፍ  ለመሰማራት ፌስቲቫሉ በር እንደከፈተላቸው ከተባበሩት አረብ ኢምሬት፣ ዮርዳኖስ፣ ግብፅ እና ቱርኪዬ የመጡ ተሳታፊዎች  ተናግረዋል።

የአፋር ክልል ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ሀላፊ ኢንጅነር ያሲን አሊ፥ ግብርናውን ከአግሮ-ኢንዱስትሪ ለማስተሳሳር የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል ብለዋል።

የፌስቲቫሉ ተሳታፊዎች ከቴምር እርሻ ጉብኝት እና ችግኝ ተከላ በተጨማሪ የአፋምቦ ሐይቅን ተመልክተዋል።

በሁሴን መሐመድ

#EBCdotstream #DatePalm #Festival #Afar #Semera