Search

በአማራ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች የተሀድሶ ስልጠናን ለመውሰድ ወደማዕከል ገቡ

ዓርብ ነሐሴ 23, 2017 50

መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ የ2ተኛ ዙር የቀድሞ ታጣቂዎች የተሀድሶ ስልጠናን ለመውሰድ በብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን የኮምቦልቻ ጊዜያዊ የተሀድሶ ማዕከልን ተቀላቅለዋል።
በትጥቅ የማስፈታት እና የተሀድሶ ስልጠና ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ም/ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን፣ የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር ተስፋዓለም ይህደጎ፣ የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎቹ ከግጭት እና ከጦርነት የሚገኝ ጥቅም አለመኖሩን ተረድተው ወደ ሰላም መንገድ መመለሳቸው የሚበረታታ መሆኑን የሀገር ሽማግሌዎች ተናግረዋል።
ለሌሎች መሳሪያ አንግበው ለሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ምሳሌ የሆነ ተግባር መሆኑንም አስረድተዋል።
የሀገር ሽማግሌዎቹ አክለውም፤ በጦርነት እና ግጭት የባከነውን እድሜ እና ሀብት መመለስ ባይቻልም፤ በቀጣይ ፊትን ወደ ልማት በማዞር የእድገቱ አካል መሆን እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለት ከ6 ዞኖች የሰላም መንገድን የተቀበሉ 1 ሺ 670 የቀድሞ ታጣቂዎች የተሀድሶ ስልጠና መውሰድ ጀምረዋል።
በአማራ ክልል በ2ኛ ዙር ከ6 ሺሕ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች ትጥቅ የማስፈታት እና የተሀድሶ ስልጠና እንደሚወስዱ ተጠቁሟል።
በመጀመርያ ዙር ከ73 ሺሕ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች ትጥቅ መፍታታቸውን እና የተሀድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ማሕበረሰቡ መቀላቀላቸውን ብሔራዊ የተሀድሶ ኮሚሽን አስታውቋል።
 
በሳምሶን ገድሉ