Search

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የእግር ኳስ ስፖርትን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከዘርፉ አመራሮች ጋር ተወያዩ

ዓርብ ነሐሴ 23, 2017 39

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ እና ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች ጋር በአዲስ አበባ ከተማ የእግር ኳስ ስፖርትን ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸዉ አግባቦች ላይ ፍሬያማ ውይይት አካሄደዋል፡፡

በዉይይቱ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፤ ከለውጡ ወዲህ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአጠቃላይ የስፖርት ዘርፍን ለማጠናከር እያከናወናቸው የሚገኙ ስራዎች አበረታች መሆናቸዉን አንስተዋል፡፡

ለዚህም 2017 በጀት አመት በአገር አቀፍ ደረጃ አንደኛ በመዉጣት እዉቅና ያሰጠዉ መሆኑን ጠቅሰዉ፤ በተለይም ታዳጊዎች ላይ ለተሰጠዉ ከፍተኛ ትኩረት ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች በበኩላቸው፤ በመጪዉ 2018 . የስፖርት ዘርፋን ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

በተለይም ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ስፖርታዊ ጨዋነትን ተላብሰዉ የታለመላቸዉን አላማ እንዲያሳኩ እና በዉጤታማነት እንዲያድግ ስፖርተኞች፣ የእግር ኳስ ደጋፊዎች፣ የስፖርቱ ማህበረሰብና ወጣቶች በየአካባቢው ያለዉ አመራር ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚናቸዉን እንዲወጡ በትጋት ለመስራት አቅደዉ ወደ ተግባር መግባታቸዉን አንስተዋል።

በውይይቱ፤ አስተዳደሩ ለስፖርቱ ዘርፍ እድገት በሰጠው ልዩ ትኩረት 1 ሺህ 530 ያህል ደረጃቸውን የጠበቁ የተለያዩ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ገንብቶ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረጉ ተገልጿል።

እንዲሁም ታዳጊ ስፖርተኞች የሚፈሩባቸው ፕሮጀክቶች እንዲስፋፉ መደረጉንና በተለይም በሁሉም የስፖርት ዘርፍ ተተኪ ምርጥ ስፖርተኞችን ማፍራት ላይ እየተሰሩ የሚገኙ ተጨባጭ ስራዎች ተጠናክረዉ እንደሚቀጥሉ ተመላክቷል።

ሁሉም ባለድርሻ አካላት ስፖርት ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለአንድነት፣ ለአገር ግንባታ የሚጫወተው ሚና ላቅ ያለ በመሆኑ ለስራው ልዩ ትኩረት በመሰጠት በትብብር መሰራቱ በስፖርቱ ዘርፍ ላይ በቀጣይም እንደ አገር እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት ሚናዉ የጎላ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ተብሏል::

ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በመቀራረብ፣ በቅንጅት እና በትብብር የላቀ ስራ ለማከናወን የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት፣ ይበልጥ ተቀራርበዉ መስራት እንደሚኖርባቸዉ መገለጹን የከንቲባ /ቤት ለኢቢሲ የላከው መረጃ ያመላክታል፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ተያያዥ ዜናዎች: